ቀጥታ፡

ብዝሃነትን በማጠናከር ክልሉን በልማት ተምሳሌት ለማድረግ ለተጀመረው ጉዞ ስኬታማነት ህዝቡ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል

ካራት፤ ህዳር 25/2018(ኢዜአ)፦ ብዝሃነትን በማጠናከር ክልሉን በልማት ተምሳሌት ለማድረግ ለተጀመረው ጉዞ ስኬታማነት ህዝቡ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

"ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደረጃ 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ማጠቃለያ በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ ተከብሯል።


 

አቶ ጥላሁን ከበደ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመረውን ሥራ ለማሳካት ህዝብን በባለቤትነት ያሳተፈ ሥራ እየተከናወነ ነው።

እንደሀገር የተጀመረው የማንሰራራት ጉዞ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸው ለዚህም የክልሉ መንግስትና ህዝብ የሚጠበቅበትን እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ ያለውን እምቅ ፀጋ በመፍጠንና መፍጠር እሳቤ አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ብዝሃነትን በማጠናከር ክልሉን በሰላምና ልማት ተምሳሌት ለማድረግ ለተጀመረው ጉዞ ስኬታማነት ህዝቡ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ድህነትና ሥራ አጥነትን በማጥፋት ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማቆየት የተጀመረው ሥራ ውጤታማ የሚሆነው በህዝቡ ተሳትፎ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አዳማ ትንጳዬ በበኩላቸው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ብዝሃነት ህገ-መንግስታዊ እውቅና እንዲያገኝ እድል ፈጥሯል ብለዋል።

በተጨማሪም ቀኑ የህዝቦች አንድነትና ልማትን ለማጠናከር እያገዘ መሆኑን ጠቅሰው፣ በክልሉ የህዝቦች አብሮነትና ሕብረብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር የጋራ ትርክትን ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቀኑ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህል፣ ወግና እሴቶች ጎልተው የሚወጡበት ነው ያሉት ደግሞ የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገሌቦ ጎልቶሞ ናቸው፡፡


 

የህዝቡን አብሮነትና ብዝሃነት ለብልጽግና ጉዞ ስኬት በመጠቀም የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ለውጤት ማብቃት ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል።

በበዓሉ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን የቀረቡ የተለያዩ ባህላዊ ትዕይንቶችም ለበዓሉ ድምቀት ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም