ቀጥታ፡

የገጠር መሬት ሃብቶችን በካዳስተር ቴክኖሎጂ መመዝገቡ ለግብርና ልማት ስራዎች ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 25/2018 (ኢዜአ):- የገጠር መሬት ሃብቶችን በዘመናዊ የካዳስተር ቴክኖሎጂ የመመዝገብ እና የማደራጀት ተግባር ለግብርና ልማት ሥራዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተገለፀ።

32 ሚሊዮን የገበሬ ማሳዎች የተለኩ ሲሆን፤ 10 ነጥብ 5 ሚሊዮን አባ ወራዎች የመሬት ይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ማግኘታቸው ተጠቁሟል።

በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ትዕግስቱ ገብረመስቀል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ሥርዓትን ለማዘመን በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል።


 

በተለይም የገጠርን መሬት ይዞታ ባለቤትነት የሚያረጋግጥ የምዝገባና የቅየሳ ሥራዎች ሲከናወን መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ይህም በመሬት አስተዳደር የነበረውን ውስንነት በመሙላት፣ የገጠር መሬት ገጽታን ለይቶ በማደራጀት በአንድ ቋት የመምራት አቅም እንዲፈጠር ማድረጉን ተናግረዋል።

በዘመናዊው የቅየሳ ሥርዓት በሀገር ደረጃ ያሉ ማሳዎች የአየር ፎቶ በመጠቀም እንዲመዘገቡ የተደረገ ሲሆን፤ ይህም የአንድ የመሬት ይዞታ ባለቤት ስም፣ የመሬት ስፋት እና መሬቱ የት እንደሚገኝ መረጃ የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ50 ሚሊዮን በላይ የገበሬ ማሳዎች እንዳሉ ጠቁመው፤ አሁን ላይ 32 ሚሊዮን የሚሆኑትን በመለየትና በመመዝገብ ለ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን አባወራዎች የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ለተመራማሪዎች እና ለውሳኔ ሰጪዎች በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ ሥርዓት መገንባቱንም ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የተገነባው ብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ ሥርዓት አሁን ላይ በ516 ወረዳዎች ተግባራዊ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

የአርሶ አደሮች የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ለውርስ፣ ለማከራየት እንዲሁም ከፋይናንስ ተቋማት የብድር አገልግሎት ማግኘት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

መሬታቸው በካዳስተር ቴክኖሎጂ የተመዘገቡ አርሶ አደሮች የእርሻ አገልግሎት የሚሰጡ ትራክተሮችና ኮምባይነሮች መግዣ ብድር ከፋይናንስ ተቋማት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የአየር ላይ ቅየሳ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ከማሁ አብርሃም በበኩላቸው፤ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በአየር ላይ ቅየሳ የኢትዮጵያ የመሬት ገጽታ በካዳስተር እየተደራጀ ነው ብለዋል።

በካዳስተር የቴክኖሎጂ ሥርዓት የተደራጁ የመሬት ገጽታ መረጃዎችንም በተቀናጀ አሠራር ለውሳኔ ሰጪ አካላት የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተለይም በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል የተለካ የገበሬ ማሳዎች ወደ ዳታ ቤዝ እንዲገባ በማድረግ፣ አርሶ አደሮች መሬት በማስያዝ ከፋይናንስ ተቋማት ብድር እንዲያገኙ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም