የኢትዮጵያ የሙያ ማህበራት ለምክክር ኮሚሽኑ ቀሪ ሥራዎች ውጤታማነት ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የሙያ ማህበራት ለምክክር ኮሚሽኑ ቀሪ ሥራዎች ውጤታማነት ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 25/2018 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ የሙያ ማህበራት ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ቀሪ ሥራዎች ውጤታማነት የበኩላቸውን ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ''የኢትዮጵያ የሙያ ማህበራት የላቀ ተሳትፎ ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት'' በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ ምክክሩን አሳታፊና አካታች ለማድረግ ለተሳታፊ ልየታ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል።
የሃይማኖት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን፣ ማህበራትን፣ ታዋቂ ሰዎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ መንግሥትንና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተወካዮቻቸው በኩል ማሳተፍ መቻሉንም ገልጸዋል።
በዚህም አብዛኛውን ሥራዎች ያከናወነ ሲሆን አሁን ላይ ወደ መጨረሻ ምዕራፍ መድረሱን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ሀገራዊ የምክክር ጉባዔውን ለማድረግ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ያሉትን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለው አማራጭ ሀገራዊ ምክክር መሆኑን ገልጸው፤ ሁሉም አካል አጀንዳዎቹን ወደ ሀገራዊ ምክክሩ በማምጣት ሊሳተፍ ይገባል ብለዋል።
ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ ከተለያዩ ማህበራት ጋር በመተባበር በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የሙያ ማህበራትም ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ቀሪ ሥራዎች ውጤታማነት የበኩላቸውን ኃላፊነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
እስካሁን የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ እንዲሳካ ላደረጉትና አሁንም እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
የተለያዩ ሙያ ማህበራትን በመወከል በውይይቱ ላይ የተሳተፉ በበኩላቸው፤ ለሀገራዊ ምክክር መሳካት ሁሉም ሊተባበር ይገባል ብለዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ዲሪብሣ ለገሠ ኮሚሽኑ እስከ አሁን ያደረጋቸው ተግባራት የሚበረታቱ መሆኑን ገልጸዋል።
ማህበሩ ችግሮች በምክክር ለመፍታት የሚያከናውነው ጥረት እንዲሳካ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አበበ በበኩላቸው፤ ማህበሩ ኮሚሽኑ ለዘላቂ ሰላም መስፈን ምክክር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር የመጡት ብራቱ ቀነኢ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ችግሮችን ለመፍታት ከምክክር ውጪ ሌላ አማራጭ ሊኖር እንደማይገባ ገልጸዋል።
ማንኛውም ዓይነት ልዩነቶች በምክክር ብቻ መፍትሄ እንደሚያገኙ ገልጸው፤ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሁላችንም አስተዋጽኦ እና ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።