በመደመር መንግሥት ዕይታ በግብርናው ዘርፍ እመርታዊ ለውጥ ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
በመደመር መንግሥት ዕይታ በግብርናው ዘርፍ እመርታዊ ለውጥ ተመዝግቧል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 25/2018(ኢዜአ)፦ በመደመር መንግሥት ዕይታ በግብርናው ዘርፍ ከቤተሰብ ፍጆታ ባለፈ ገበያ ተኮር ምርቶችን በዓይነት፣ በምርት ብዛትና በጥራት የማምረት እመርታዊ ለውጥ መመዝገቡን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በመደመር መንግሥት መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት፣ በኢትዮጵያ ባለፉት አስርት ዓመታት የተሰራው የግብርና ልማት በአነስተኛ የገበሬ ማሳ ላይ ያተኮረ ነበር።
የግብርና ልማቱ ትርፍ ምርት ማምረት ባያስችልም የቤተሰብ የነፍስ ወከፍ ገቢን በማሳደግ ረገድ ለውጥ አሳይቷል።
ነገር ግን የግብርናው ዘርፍ ከቤተሰብ ፍላጎት ተሻግሮ የገበያና የኢንዱስትሪውን ፍላጎት ማሟላት የሚያስችል ትርፍ ምርት እንዲያመርት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመፅሐፋቸው አንስተዋል።
በአነስተኛ ይዞታና ደረጃ የሚከናወን ግብርና ልማት ዘርፉን እንደማያሻግረውም አመላክተዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን(ዶ/ር) የኢትዮጵያ የመሬት ይዞታ የተበጣጠሰ በመሆኑ ለገበያ የሚሆኑ ምርቶችን ማምረት አዳጋች ነው የሚሉ የተዛቡ አስተሳሰቦች ከዚህ ቀደም እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ይህን አስተሳሰብ የቀየሩ ተጨባጭ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።
በመደመር መንግሥት የግብርና ዘርፍ ዕይታም በኩታ ገጠም እርሻ አነስተኛ ማሳ ያላቸውን አርሶ አደሮች በማቀናጀት ከራስ አልፎ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን እንዲያመርቱ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
መደመር አቅሞችን አውቆ፣ አሰባስቦና፣ አከማችቶ የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ማረጋገጥ መሆኑንም አንስተዋል።
አሁን ላይ አርሶ አደሩ ከራስ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ እንዲሁም ለኢንዱስትሪ መቅረብ የሚችሉ ምርቶችን በአይነት፣ ብዛትና በጥራት ማምረት መቻሉን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሤ(ዶ/ር)፥ የግብርና ዘርፉን ምርትና ምርታማነት የበለጠ ለማሳደግ የሥራና የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
ግብርናውን ለማሻገር ጊዜን፣ ቴክኖሎጂንና የሰው ኃይልን በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህ ደግሞ የተሰባሰበ አቅምና ትብብርን ማጎልበት ተገቢ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አመራሮቹ አክለውም የመደመር መንግሥት በተከተለው አዲስ ዕይታ በመንግሥት፣ በአርሶ አደሩ፣ በባለሀብቶችና በልማት አጋሮች መካከል የግብርና ትብብር ከመቼውም ጊዜ በላይ መጠናከሩን ገልጸዋል።
ይህም የግብርናም ሆነ አጠቃላይ የገጠር ሽግግር ቅንጅትን እንደሚጠይቅ በመደመር መንግሥት መፅሐፍ የተጠቀሰውን እሳቤ ያሳየ ነው ብለዋል።
መንግሥት የዘርፉን ተዋናዮች አቅም በማቀናጀትና ግብርናን ወደ ኢንቨስትመንት ማዕከልነት በማሸጋገር ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡና በርካታ አርሶ አደሮችም ወደ ኢንቨስተርነት እየተሸጋገሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።