ቀጥታ፡

በክልሉ ያለውን እምቅ የቱሪዝም ሀብት በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው

ሚዛን አማን ፤ ሕዳር 25/2018 (ኢዜአ):- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ያለውን እምቅ የቱሪዝም ሀብት በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በአንድ ወረዳ አንድ መስህብ ለማልማት አቅጣጫ ተቀምጦ ወደተግባር መገባቱም ተመላክቷል። 

የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ መንግስት በገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት አማካኝነት የክልሉን የቱሪዝም ትንሣኤ ማብሰሩን አስታውሰዋል። 


 

በዚህም በክልሉ የተገነቡ ሀላላ ኬላ፣ ዝሆን ዳና ሎጅ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መንግስት ለቱሪዝም ልማት ያሳየውን ቁርጠኝነት ተከትሎም በክልሉ ያሉ ዞኖች በራስ አቅም የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን የማልማት ሥራ መጀመራቸውን አቶ ፋንታሁን ጠቁመዋል።

ከዘርፉ እመርታዊ ለውጥ ለማምጣትና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በቀጣይም የቱሪስት መዳረሻዎችን የማስፋፋት ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በክልሉ ሰፊ የተፈጥሮ፣ ባህላዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም ጸጋዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ከእነዚህ ውስጥ ባላቸው አቅም በጥናት የተለዩትን 11 ጸጋዎች ቀድሞ ለማልማት ይሰራል ብለዋል።


 

አቶ ፋንታሁን እንዳሉት፤ ክልሉ ካሉት እምቅ መስህቦች መካከል የሕዝቦች ባህል፣ የቡና ቱሪዝም ከማሳ እስከ ስኒ፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ከምርት እስከ ቅንብር፣ የዱር አራዊት፣ በዩኔስኮ የተመዘገቡ የተፈጥሮ ደኖች ከበርካታ ፏፏቴዎች ጋር ተጠቃሾች ናቸው።

አንድ ወረዳ አንድ የቱሪስት መስህብ እንዲያለማ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በክልሉ ከ61 በላይ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን በዚህ ዓመት ለማልማት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አመልክተዋል።

በዚህም በመዳረሻዎቹ አካባቢ መንገድ የመክፈትና መለስተኛ የእንግዳ ማረፊያ በማዘጋጀት ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ሥራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።


 

መስህቦቹን ከማልማት በተጨማሪ በዘርፉ ለወጣቶች የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የማሳደግ ግብ መቀመጡን አመልክተዋል።

ወደእነዚህ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች ጎብኚዎች እንዲመጡ ለማድረግ ከልማት ሥራው ጎን ለጎን ቢሮው በተለያዩ አማራጮች የማስተዋወቅ ሥራ እያከናወነ መሆኑንም አቶ ፋንታሁን ተናግረዋል።

ሰሞኑን ለመንግስት ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በተሰጠ ስልጠና ማጠቃለያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት ገለጻ፣  በክልሎች እንደየ አካባቢው ያለን ሀብት ለይቶ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚጠበቅ ማስገንዘባቸው የሚታወስ ነው።


 

በዚህም በክልሉ በተለይ በአንድ ግቦች የተቀመጠውን መርህ መነሻ በማድረግ አንድ ወረዳ አንድ መስህብ እንዲያለማ መደረጉ በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በአንድ ዞን የተለያዩ የቱሪስት መስህቦች እንዲጎበኙ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አቶ ፋንታሁን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም