በክልሉ ፖሊስ ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል የሕዝብ አገልጋይነቱን ለማጎልበት የጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ፖሊስ ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል የሕዝብ አገልጋይነቱን ለማጎልበት የጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ ይቀጥላል
ባሕር ዳር ፤ ሕዳር 25/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ፖሊስ የሙስናና ሌሎች ወንጀሎችን አስቀድሞ በመከላከል የሕዝብ አገልጋይነቱን ይበልጥ ለማጎልበት የጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለጹ።
''ትውልድን በስነ ምግባር፤ ተቋምን በአሰራር'' በሚል መሪ ሀሳብ የክልሉ የፖሊስ አመራሮችና አባላት የተሳተፉበት የፀረ ሙስና ቀን ዛሬ በባሕርዳር ከተማ ተከብሯል።
በዚህ ወቅት የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፤ ሙስናና ብልሹ አሰራርን መከላከል የፖሊስ ዋና ተግባር ነው ብለዋል።
ሙስና የግል ጥቅምን በማስቀደም ፍትሃዊ አሰራርንና ተጠቃሚነትን የሚያዛባ ፣ ሕዝብና ሀገርን የሚጎዳ ተግባር እንደሆነ አንስተዋል።
ይህንን መከላከል ፖሊስ ግንባር ቀደም ተግባሩ በመሆኑ ከብልሹ አሰራር በመራቅ እና መልካም ስነ ምግባር በመላበስ መትጋት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።
ብልሹ አሰራርንና ሙስናን መከላከል የሚያስችል ተቋማዊ ሪፎርም እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ባጠረ ጊዜ ተስፋ ሰጭ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ፖሊስ የሙስናና ሌሎች ወንጀሎችን አስቀድሞ በመከላከል የሕዝብ አገልጋይነቱን ይበልጥ ለማጎልበት የተጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮሚሽነር ዘላለም (ዶ/ር) አረጋግጠዋል።
ሙስናና አድሏዊ አሰራር ከሕዝብ የተሰወረ ባለመሆኑ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሕብረተሰቡም አጥፊዎችን በማጋለጥ ሚናውን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበትም አንስተዋል።
በመድረኩ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ሙስናን በዘላቂነት ለመከላከል የትውልድ ስነ ምግባር ግንባታ ላይ ማተኮር ይገባል ብለዋል።
በትውልድ ግንባታ ሂደቱ የስነ ምግባር እሴትን ማጠናከርና ማስተማር ትኩረት እንዲሰጠው ጠቁመዋል።
ሙስናን መከላከል የምርጫ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በክልሉ የተጀመረው የፖሊስ ተቋማዊ መዋቅር ሙስናን ለመከላከል የሚያስችል ነው ብለዋል።
በጠቅላይ መምሪያው የወንጀል ምርመራ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው፤ ሙስናን ለመከላከል የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶ እየተተገበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም ከሕዝብ የሚደርስ የሙስና ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ የመመርመርና የማጣራት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል። ።