ቀጥታ፡

አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት ልዩ ልዩ የቤት ልማት መርሃ ግብር ነድፎ ተግባራዊ እያደረገ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 25/2018 (ኢዜአ):-የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት ልዩ ልዩ የቤት ልማት መርሃ ግብር ነድፎ ተግባራዊ እያደረገ ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአስተዳደሩ እና በሌጋሲ ሆም የመንግስትና የግል አጋርነት በላፍቶ ሳይት የሚገነባ የመጀመሪያ ምዕራፍ የ26 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ አስጀምረዋል።

ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ አስተዳደሩ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግቶ እየሰራ ነው።


 

የነዋሪዎች ቁልፍ ጉዳይ የሆነውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ልዩ ልዩ የቤት ልማት መርሃ ግብር ነድፎ ተግባራዊ እያደረገ ነው ብለዋል።

ዛሬ በይፋ ወደ ስራ የገባው የቤት ግንባታ በዓይነቱ በሀገርም ሆነ በከተማ ደረጃ አዲስና የመጀመሪያ የሆነ ቴክኖሎጂ እንደሚጠቀም ተናግረዋል።


 

ግንባታው ጋልቫናይዝድ የብረት ውጤት በመጠቀም እስከ 12 ወለሎች የሚደርሱ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ባጠረ ጊዜ መገጣጠም የሚያስችል እንደሆነም አስታውቀዋል። ይኸው ፋብሪካ በሙሉ አቅም ወደ ስራ ሲገባ 26 ሺህ ቤቶችን በዓመት መስራት እንደሚችል ገልጸዋል።  

ቤቶቹ ከዚህ ቀደም ከሚታወቀው የመኖሪያ ቤቶች በብዙ እጅ የተሻለ የቆይታ ዘመን እንደሚኖራቸው አመልክተው፤ ይህም የከተማዋን ነዋሪዎች የቤት ፍላጎት ለማሟላት የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አብራርተዋል።


 

ከዚህ በተጨማሪም ፋብሪካው ቤቶችን ለዜጎች ኢኮኖሚያዊ በሆነ መንገድ፣ በላቀ ጥራት እንዲሁም በፍጥነት ማድረስ የሚያስችል አዲስ የህንጻ ግንባታ አሰራርን ዕውን የሚያደርግ በመሆኑ በግንባታ ወቅት ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር አብራርተዋል።

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ  ቅድስት ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ዛሬ የተጀመረው የቤት ግንባታ የቤት ልማት መርሃግብሩን ሁሉን አቀፍና ተደራሽ በማድረግ ለዜጎች የተሻለ መጠለያን ለማጎናፀፍ አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።


 

አስተዳደሩ የቤት ልማት መርሃ ግብሩን የሚያቀላጥፉ ቴክኖሎጂዎችን ከሁሉም አቅጣጫ በማፈላለግ የመኖሪያ ቤት ተደራሽነት ላይ ትኩረት አድርጓል ያሉት ኃላፊዋ፤ በዚህም ተጨባጭ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።

ይህን የቤት ግንባታ ሳይትም ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር በመፍጠርና በመፍጠን መርህ ባጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ ቃል ገብተዋል።


 

የሌጋሲ ሆም ባለቤት ያሬድ አፈወርቅ በበኩላቸው፤ ግንባታው የኮልድ ፎርምድ ስቲል (Cold-Formed Steel (CFS) ቴክኖሎጂን በመጠቀም በፍጥነትና በጥራት ቤት ለመገንባት የሚያስችል  ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም