በክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ኃብት በማልማት የታለሙትን የልማት ግቦች ለማሳካት እንሰራለን - አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ኃብት በማልማት የታለሙትን የልማት ግቦች ለማሳካት እንሰራለን - አመራሮች
ጋምቤላ ፤ ሕዳር 25/2018 (ኢዜአ):- በክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ኃብትና ሰፊ የሰው ኃይል በማስተባበር የታለሙትን የልማት ግቦች ለማሳካት እንደሚሰሩ የጋምቤላ ክልል አመራሮች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ’’በመደመር መንግስት እይታ የዘርፎች እመርታ’’ በሚል መሪ ሃሳብ ለከፍተኛ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠናና የስራ አቅጣጫ መስጠታቸው ይታወሳል።
በሁሉም አካባቢዎች አቅሞችን በማካበት በመፍጠርና በመፍጠን ለላቀ እመርታና ማንሰራራት መስራት እንደሚገባም አፅዕኖት ሰጥተዋል።
በተለይም በግብርና እና ገጠር ልማት ትራንስፎርሜሽን፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ፣ በከተማ ልማትና በሌሎችም ዘርፎች የተያዙ የልማት ግቦችን በማስረዳት ለተግባራዊነታቸው በትብብር መትጋት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በጋምቤላ ክልል ያለውን ዝግጁነትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በተመለከተ ኢዜአ የተለያዩ አመራሮችን አነጋግሯል።
ከክልሉ አመራሮች መካከል አቶ ሙሉጌታ ሩድ፤ በዘርፎች እመርታ ዙሪያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠና እና የስራ አቅጣጫ ለለውጥና ማንሰራራት ወሳኝ መሆኑን የተረዳንበት ነው ብለዋል።
በመሆኑም በክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ኃብትና ሰፊ የሰው ኃይል በማስተባበር የታለሙትን የልማት ግቦች ለማሳካት የላቀ ዝግጁነት አለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
በክልሉ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ቢኖርም ማልማት ካልተቻለ ህዝብን ተጠቃሚ አያደርግም ያሉት አቶ ሙሉጌታ የአመለካከትና የተግባር አንድነታቸውን በማጎልበት ያለውን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት በማልማት የህዝቡን ህይወት ለመለወጥ ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የአቅም ግንባታ ስልጠናውና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጡ አቅጣጫዎች ሀገርና ህዝብን የሚቀይር እሳቤ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የክልሉ አመራር አቶ አብርሃም ማይክል ናቸው።
በመሆኑም በአቅም ግንባታ ስልጠናው ያገኙትን አቅም በመጠቀም በክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ጸጋዎችና ሰፊ የሰው ኃይል አስተባብረው በቁጭት በመስራት የህዝቡን ህይወትና አካባቢያቸውን ለመለወጥ ተግተው እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ሌላኛው አመራር አቶ ቢየ ቶክ እንደገለጹት፤ የአመራር ስልጠናው እንደ ሀገር የተጀመሩ የልማት ግቦችን ለማሳካት ትልቅ አቅምና ተነሳሸነትን የሚያጎለበት ነው።
በመሆኑም ያገኙትን የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደ ግብዓት በመጠቀም ለክልሉ ልማትና እድገት ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።