ቀጥታ፡

በሰመራ-ሎጊያ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማዋን የኢንቨስትመንትና የቱሪስት መዳረሻነት ይበልጥ ያሳድገዋል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 25/2018 (ኢዜአ):-በሰመራ-ሎጊያ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ከምቹ መኖሪያነት ባለፈ የኢንቨስትመንትና የቱሪስት መዳረሻነቷን ይበልጥ የሚያሳድግ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ አብዱ ሙሳ ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ከተሞችን ምቹ የመኖሪያ፣ የኢኮኖሚ ማዕከልና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት አሁን ከ70 በላይ በሚሆኑ የሀገሪቱ ከተሞች በመከናወን ላይ ይገኛል።

የኮሪደር ልማቱን እየተገበሩ ከሚገኙ ከተሞች መካከል የአፋር ክልል ርዕሰ ከተማ የሆነችው ሰመራ-ሎጊያ አንዷ ናት።


 

የከተማዋ ከንቲባ አብዱ ሙሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የኮሪደር ልማቱ በሦስት ምዕራፎች እየተከናወነ ነው።

የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ መጠናቀቁን ገልጸው፤ ቀሪዎቹንም ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማቱ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ፣ ፓርኮች፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኃይል መሙያ እንዲሁም የክልሉን ባህላዊ እሴቶች በጉልህ የሚያሳዩ ግንባታዎችን ያካተተ መሆኑን አንስተዋል።


 

የመሰረተ ልማት ግንባታዎቹ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸው፤ ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት 30 በመቶ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ  የሚያደርጉ እንዲሁም የቱሪስት እና የኢንቨስትመንት መዳረሻነቷን የሚያጎለብቱ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

በዚህም የከተማዋን የወጪና ገቢ ንግድ ማዕከልነት የሚመጥኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

የክልሉ መንግሥትና ከተማ አስተዳደሩ ሰመራ-ሎጊያ ከተማን ውብና ማራኪ፣ አረንጓዴ እንዲሁም ለቱሪስቶች ምቹ ለማድረግ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የከተማዋ ነዋሪ የሆነው ወጣት ሀቢብ መሀመድ፤ ሰመራ-ሎጊያ በከፍተኛ ለውጥ ውስጥ እንደምትገኝ በመጥቀስ በተለይም በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ስራዎች ምቹ የመኖሪያና የመዝናኛ ስፍራን እየፈጠሩ መሆኑን ተናግሯል።


 

የልማት ስራዎቹ ወጣቶች ከተማዋ ያላትን ተስፋ እንዲመለከቱና ለለውጥ እንዲተጉ የሚያነሳሱ ናቸው ብሏል።

የከተማዋ ነዋሪ ወጣት መይረም መሐመድ በበኩሏ፤ በከተማዋ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ገጽታዋን በመቀየር ውበት እንድትላበስ ከማድረጉ ባሻገር ለህብረተሰቡ ምቹ ከባቢን መፍጠሩን ገልጻለች።


 

በተጨማሪም በከተማዋ ለእግረኛ  ምቹ መንገድ እንዳልነበር በማንሳት የኮሪደር ልማቱ ችግሩን እየቀረፈ መሆኑን ጠቅሳለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም