ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ የተሻሻለውን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ  አጸደቀ

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 25/2018 (ኢዜአ):- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሻሻለውን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ  አጸደቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአምስተኛ ዓመት የስራ ዘመን ሶስተኛ መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችንና የብድር ስምምነቶችን አጽድቋል።

ከጸደቁ ረቂቅ አዋጆች መካከል የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011ን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።

የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዕጩዎች ምዝገባ ጋር በማያያዝ ያነሱት የነበረውን ቅሬታ በመፍታት ለሰባተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሏል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በኢትዮጵያና  በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለዘላቂ እና ንፁህ የኢነርጂ ተደራሽነት ለውጥን ለማፋጠን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ በተደረገው የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል፡፡

እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለምስራቅ አፍሪካ የክህሎት ትራንስፎርሜሽን እና ቀጣናዊ ውህደት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል ተጨማሪ የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅንም አጽድቋል።

በኢትዮጵያና ቻይና መንግሥት መካከል የተደረገውን የወንጀል ጉዳዮች የጋራ የሕግ ትብብር ስምምነት እንዲሁም ፍርደኞችን የማስተላለፍ ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ለዝርዝር እይታ ለሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያና በብራዚል መካከል የተደረገውን ፍርደኞችን የማስተላለፍ ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን  እና በኢትዮጵያ እና የደቡብ አፍሪካ መንግሥታት መካከል የተደረገውን በወንጀል ጉዳይ የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም