ቀጥታ፡

ሆስፒታሉ አገልግሎቱን በማሻሻሉ ከእንግልት ታድጎናል - ተገልጋዮች 

አሶሳ፤ ህዳር 25/2018 (ኢዜአ)፦ የከማሺ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻሉ ከእንግልት ታድጎናል ሲሉ የሆስፒታሉ ተገልጋዮች ተናገሩ። 

የከማሺ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፤ ሆኖም በአካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት በመኖሩ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት እንቅፋት ሆኖበት እንደቆየ ተመልክቷል። 

ባለፈው ዓመት ግን ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ባገኘው የሶላር ኃይል አማራጭ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱ እየተሻሻለ መጥቷል።


 

በሆስፒታሉ የወሊድ አገልግሎት ለማግኘት የመጡት ወይዘሮ ሎምጨ ጀቤሳ ፤ የአገልግሎት አሰጣጡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

በአካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመኖሩ ከዚህ ቀደም በሆስፒታሉ አገልግሎት ለማግኘት ስንመጣ በመጉላላት እና ተገቢውን ህክምና ሳናገኝ እንመለስ ነበር ያሉት ወይዘሮ ሎምጨ አሁን ግን የተገጠመው ሶላር በፈለግነው ሰዓት ህክምና እንድናገኝ አግዞናል ብለዋል።

ለወሊድ ወደ ሆስፒታሉ በመጡበት ወቅት የባለሙያዎች ዕገዛ እንዳልተለያቸውና መንታ ወንድ ልጆችን በሠላም መገላገላቸውን ገልጸዋል።

ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ ስራ በመጀመሩ ለተሻለ ህክምና ወደ አሶሳ ይሄዱ የነበሩ ታካሚዎችን ከወጪ እና እንግልት እየታደገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።


 

በሆስፒታሉ እናቷን በማሳከም ላይ የነበረችው ወጣት እናቴ ዮናታ ደግሞ በሆስፒታሉ በነበራቸው የስድስት ቀናት ቆይታ ባለሙያዎቹ አስፈላጊውን መድኃኒት እና የህክምና ክትትል ሲያደርጉ ማየቷን ገልጻለች።

ሆስፒታሉ በተለይ የሶላር ኃይል ከተገጠመለት በኋላ የአገልግሎት አሰጣጡ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልፃ ሆስፒታሉ ለአካባቢው ማህበረሰብ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ ነው ብላለች።


 

የከማሺ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር እና ጠቅላላ ሐኪም ዶክተር ስመኘው ገብሬ በበኩላቸው፤ ሆስፒታሉ የተሻለ አገልግሎት እንዳይሰጥ የኃይል አቅርቦት እጥረት ፈተና ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ችግሩን በመረዳት የገጠመው የሶላር ኃይል የሆስፒታሉን አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል ህብረተሰቡ ተገቢውን ህክምና እንዲያገኝ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም