ቀጥታ፡

የንግድ በዛሩና አውደ ርዕዩ ምርቶችን ለማስተዋወቅና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ምቹ እድል ፈጥሯል

ወልቂጤ፤ ሕዳር 25/2018 (ኢዜአ)፦የንግድ በዛሩና አውደ ርዕዩ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ምቹ እድል መፍጠሩን ኢንተርፕራዞችና ማህበራት ገለጹ፡፡

20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን በማስመልከት በወልቂጤ ከተማ የንግድ ባዛርና አውደ ርዕይ እየተካሄደ ነው።

በባዛሩ ላይ የተሳተፉ ኢንተርፕይዞችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደገለጹት፤ ባዛሩ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ፣ የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማጠናከርና የገበያ ትስስር ለመፍጠር አግዟቸዋል።

በንግድና ባዛሩ ከተሳተፉ የኢንተርፕራይዝ ባለቤቶች መካከል ከስልጤ ዞን የመጣችው ወይዘሪት አክራም አዝማች፤ የባህል አልባሳት ይዛ መቅረቧን ገልጻለች፡፡


 

በዚህም የክልሉን ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህል ከማስተዋወቅ ባለፈ ምርቶቿን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሆነችና አዳዲስ የገበያ ትስስር መፍጠሯን ነው ያስረዳቸው፡፡በዓሉ ለብዙዎች የሥራ እድልም እየፈጠረ መሆኑን ተናግራለች፡፡

ከሆሳዕና ከተማ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ይዘው በባዛሩ ላይ እየተሳተፉ ያሉት አቶ ተሻለ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በባዛሩ ባገኙት የገበያ እድል በኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት።


 

ከገበያ እድል ባለፈ የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማጠናከርና የባህል ልውውጥ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከወልቂጤና ሃላባ ቁሊቶ ከተማ የባልትና ውጤቶችን ይዘው የተሳተፉት ኢንተርፕራይዞች በበኩላቸው፤ የንግድ ባዘሩና አውደ ርዕዩ አምራቹን ከሸማቹ በማገናኘት ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢንርፕራይዞቹ ሰብሳቢዎች ወጣት ፀጋዬ ብዛ እና አብራክ ወልደጊዮርጊስ፤ በዓሉ ኢትዮጵያዊያን ካሉበት በመሰባሰብ ደምቀው የሚታዩበት ብቻ ሳይሆን የሚገበያዩበትንም እድል ይዞ መምጣቱንም ገልጸዋል።


 

ለበዓሉ በወልቂጤ ከተማ የተከፈተው የንግድ ባዛርና አውደርዕይ ምርቶቻቸውን በስፋት ለማቅረብና የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡ 

በባዛሩ ላይ ግብይት ሲፈጽሙ የነበሩት አቶ ፈቀደ ደድገባ እና ወይዘሮ ጸጋነሽ ኮርማ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ባዛሩ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ መከፈቱ የተለያዩ ባህላዊ አልባሳትና ቁሶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በቅርበት ለመሸመት አስችሏቸዋል።

እርስ በርስ የባህል ልውውጥ ለማድረግ እያገዘ መሆኑንም ነው ጠቅሰዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ፤ የንግድ ባዛርና አውደ ርዕዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እሴቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በባዛሩ ከ200 በላይ አምራቾችና ነጋዴዎች መሳተፋቸውን ጠቁመው የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የእደ ጥበብ ውጤቶችም መቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

እስከ ህዳር 27 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆየው ባዛርና አውደርዕይ የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ ልምድ ለመለዋወጥና የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንዳለውም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም