ቀጥታ፡

ኢጋድ እና ተመድ በቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 25/2018(ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ስራቸውን ይበልጥ የተቀናጀ ለማድረግ እንደሚሰሩ አስታወቁ።   

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጉዋንግ ኮንግ ጋር በአዲስ አበባ ተወያይተዋል።

ውይይቱ ኢጋድ እና ተመድ በሰላም፣ ደህንነት እና የሰብዓዊ ጉዳዮች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ነው።

ኢጋድ፣ የአፍሪካ ህብረት እና ተመድ ለተረጋጋ ቀጣና የተቀናጀ የሶስትዮሽ አካሄድ ለመከተልም የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።

ኢጋድ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ከሁሉም አጋሮች ጋር በመሆን ሰላማዊ፣ ደህንነቱ የተረጋገጠ እና የማይበገር የአፍሪካ ቀንድ ለመፍጠር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ መግለጻቸውን ኢዜአ ከኢጋድ ሴክሬተሪያት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በይፋ አጋርነት የመሰረቱት እ.አ.አ በ2015 መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም