ቀጥታ፡

አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እየሰራ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 25/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እየሰራ ይገኛል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአስተዳደሩ እና በሌጋሲ ሆም የመንግስትና የግል አጋርነት በላፍቶ ሳይት የሚገነባ የመጀመሪያ ምዕራፍ የ26 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ አስጀምረዋል።

በመርኃ ግብሩ ላይም የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።


 

ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ አስተዳደሩ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግቶ እየሰራ ነው።

የነዋሪዎች ቁልፍ ጉዳይ የሆነውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ልዩ ልዩ የቤት ልማት መርሃ ግብር ነድፎ ተግባራዊ እያደረገ ነው ብለዋል።

ዛሬ በይፋ ወደ ስራ የገባው የቤት ግንባታ በዓይነቱ በሀገርም ሆነ በከተማ ደረጃ አዲስና የመጀመሪያ የሆነ ቴክኖሎጂ እንደሚጠቀም ተናግረዋል።


 

ግንባታው ጋልቫናይዝድ የብረት ውጤት በመጠቀም እስከ 12 ወለሎች የሚደርሱ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ባጠረ ጊዜ መገጣጠም የሚያስችል እንደሆነም አስታውቀዋል።

ይኸው ፋብሪካ አሁን ባለው ሙሉ አቅም ወደ ስራ ሲገባ 26 ሺህ ቤቶችን በዓመት መስራት እንደሚችል ገልጸዋል።  


 

ቤቶቹ ከዚህ ቀደም ከሚታወቁት የመኖሪያ ቤቶች በብዙ እጅ የተሻለ የቆይታ ዘመን እንደሚኖራቸው አመልክተው፤ ይህም የከተማዋን ነዋሪዎች የቤት ፍላጎት ለማሟላት የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አብራርተዋል።


 

ከዚህ በተጨማሪም ፋብሪካው ቤቶችን ለዜጎች በላቀ ጥራት እንዲሁም በፍጥነት ማድረስ የሚያስችል አዲስ የህንጻ ግንባታ አሰራርን ዕውን የሚያደርግ በመሆኑ በግንባታ ወቅት ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም