ቀጥታ፡

ጥራት ያለው ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በተከናወኑ ሥራዎች በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 25/2018 (ኢዜአ)፡- በበጀት ዓመቱ ያለፉት ወራት ተገማችና ግልጽ የኢንቨስትመንት ከባቢ በመፍጠር ጥራት ያለው ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በተከናወነ ሥራ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸው ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢኮኖሚ ማሻሻው ባስገኛቸው ውጤቶችና ተቋማችን ተገማችና ግልጽ የኢንቨስትመንት ከባቢ በመፍጠር ጥራት ያለው ኢንቨስትመንት ለመሳብ ባከናወናቸው ተግባራት በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

በዚህም በ2018 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ961 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን አረጋግጠዋል።

በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ከሚገኙ ኢንቨስትመንቶች ከወጪ ንግድ ከ49 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም አንስተዋል።

ኮሚሽኑ በሩብ ዓመቱ 123 የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን ጠቅሰው፤ ፈቃድ ከተሰጣቸው የውጭ ባለሀብቶች መካከል 34ቱ በቅርቡ ክፍት በሆነው በገቢና ወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን ማውጣት፣ ቱሪዝም እና አይሲቲ ዘርፎች ለባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች እየተሰጡ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ገቢና ወጪ ንግድን ጨምሮ በፋይናንስ ዘርፍና በተለያዩ ሴክተሮች ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ መዋለ-ነዋያቸውን እንዲያፈስሱ እየተሠራ መሆኑን ኮሚሽነሩ አመላክተዋል።

በአጠቃላይ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ በወጪ ምርቶች፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ፈቃድ የወሰዱ ፕሮጀክቶችን ወደ ማምረት ለማሸጋገር እና በቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ስኬቶች መመዝገባቸውን ነው ያነሱት።

በቀጣይም የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠል እና በክፍተት ለተለዩ ጉዳዮች መፍትሔ በመስጠት ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ እድገት እና ብልጽግና የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም