የወንድማማችነትና የእህትማማችነት እሴትን ለማጠናከር ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የወንድማማችነትና የእህትማማችነት እሴትን ለማጠናከር ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል
ሆሳዕና ፤ ሕዳር 25/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወንድማማችነትና የእህትማማችነት እሴትን በዘላቂነት ለማጠናከር የተጀመረውን ጥረት እውን ለማድረግ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)ገለጹ፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ በክልሉ የሚከበረውን 20ኛው የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓልን በማስመልከት የተዘጋጀ የማስ ስፖርትና የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ውድድር በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል፡፡
በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እንዳመለከቱት፤ ስፖርት የማህበረሰብን ትስስር ለማጠናከርና የወንድማማችነት እሴት እንዲጎለብት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው።
በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት በተደረገበት ዋዜማ የሚደረግ የአካል ብቃት እንቅስቃሴና የሩጫ ውድድር ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
የወንድማማችነትና የእህትማማችነት እሴትን በዘላቂነት ለማጠናከር የተጀመረውን ጥረት እውን ለማድረግ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ክልሉ የሚያስተናግደውን 20ኛው የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓልን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን በመቀበል የአብሮነት እሴቶች እንዲጠናከሩ የበኩላቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሾ በበኩላቸው፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴውና የሩጫ ውድድሩ ዓላማ በክልሉ የተጀመሩ ፈጣን የለውጥ ጉዞን ለማጠናከር ማህበረሰቡን ያሳተፈ ተግባርን ማከናወን መሰረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ስፖርት የአብሮነት እሴትን ለማጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በሁሉም መዋቅሮች የተለያዩ ስፖርታዊ ክንዋኔዎች ሲደረግ ስለመቆየቱም አንስተዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎን ጨምሮ ሌሎችም የክልል ፤ የዞን ፤ የሆሳዕና ከተማ ከፍተኛ አመራሮችና የከተማው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡