ቀጥታ፡

በመደመር መንግስት የብዝኀ ዘርፍ ዕይታዎች የኢትዮጵያን ብልጽግና አይቀሬ መሆኑን ማረጋገጫ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 24/2018(ኢዜአ)፦ በመደመር መንግስት የብዝኀ ዘርፍ ዕይታዎች የኢትዮጵያ ብልጽግና አይቀሬ  መሆኑን እንደሚያረጋግጡ የመንግስትና የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሃሳብ ለቀናት ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባላት የማጠቃለያ ስልጠና መስጠታቸው ይታወሳል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሥልጠናው ላይ  እንደገለጹት፤ የመደመር መንግስት የሚፈጽማቸው የልማት ግቦች የሁሉንም ዜጋ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ነው ያረጋገጡት።

የኢትዮጵያን ቀደምት ስልጣኔና ቀጣይ መዳረሻ ታሳቢ በማድረግም በመደመር መንግስት የመፍጠን፣ መፍጠር፣ ማባዛትና ማጥራት እሳቤ ለከፍተኛ አመራሩ አብራርተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሐመድ እድሪስ (ዶ/ር)፤ የመደመር መንግስት ኢትዮጵያ ትመራበት ከነበረ የተውሶ ሃሳብ በማላቀቅ ስኬታማ ስራዎችን እየሰራ ነው ብለዋል።


 

የመደመር እሳቤም ከርዕዮተ ዓለማዊ ታማኝነት ወደ ህዝብና ሀገርን ማገልገል ታማኝነት፣ አካታች ካልሆነ የፓርቲ፣ የተቋምና የልማት ፖሊሲ እሳቤ ወደ አቃፊነት መቀየር እንዳስቻለ ተናግረዋል።

የከፍተኛ አመራር አባላት ስልጠናም በጠራ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ልማትን ማሳካት የሚያስችል ተግባቦት የተፈጠረበት መሆኑን ገልጸዋል።

የመደመር መንግስት ከሃሳብና ተቋም በመነሳት ሽግግርን በስኬት በመምራት የጸና መንግስት በመገንባት የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት የተፈጠረበት መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ብዝኀ ዘርፍ ዕይታዎች የኢኮኖሚ ስኬት የመደመር መንግስት ወሳኝ ትሩፋት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የብዝኀ ኢኮኖሚ ሥርዓቱም አንደኛው የሌላኛው የልማት ደጀን መሆን አስችሏል ብለዋል።

የብዝኀ ዘርፍ የልማትም የኢትዮጵያን ብዝኀ ጸጋና አቅሞች በማሰባሰብ በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ዲጂታል ሥርዓት ስኬቶችን ያመጣ የመደመር መንግስት ኢኮኖሚያዊ እሳቤ መሆኑን ገልጸዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ስሑል በበኩላቸው፤ የመደመር መንግስት መንገዱን መደመር መዳረሻው ደግሞ የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ መርህ ያደረገ ነው ብለዋል።


 

ባለፉት ጥቂት ዓመታትም በጠራ የመደመር መንግስት እሳቤ ትላልቅ ውጤቶችን በማስመዝገብ ለበርካታ ሀገራት ጭምር አርዓያ መሆን የቻለ ስኬት መምጣቱን አስረድተዋል።

የብዝኀ ዘርፍ ኢኮኖሚ ልማት የኢትዮጵያን የመልማት አቅም ወደ ጥቅም የቀየር ሀገር በቀል የዕድገት እሳቤ ነው ያሉት አቶ ነብዩ፤ የብዝኀ ዘርፍ የኢኮኖሚ ሥርዓቱም የተሟላ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ መሠረት እየጣለ መሆኑን ገልጸዋል።

የብዝኀ ዘርፍ የኢኮኖሚ ሥርዓትም የመንግስት፣ የህዝብና የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ የብዝኀ ተዋናይነት ሚና በማስፋት ውጤት ማምጣቱን አንስተዋል።

ለአብነትም የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገርን ብልጽግና አይቀሬነት በሚያረጋግጥ መልኩ ዕድገት እያስመዘገበ መቀጠሉን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም