ቀጥታ፡

የተከናወኑ ሪፎርም ስራዎች በሰው ሀብት ልማት ላይ የተሻለ ለውጥ እንዲመዘገብ አስችለዋል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 24/2018 (ኢዜአ)፦በሥራና ክህሎት ልማት የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች በሰው ሀብት ልማት ላይ የተሻለ ለውጥ እንዲመዘገብ ማስቻሉን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደር ቢሮዎች እንዲሁም ተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ለሶስት ቀናት በቢሺፍቱ ከተማ ያካሄደውን የምክክር መድረክ አጠናቋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፤ የሰው ሃብት ልማትን ለማሻሻል የተከናወኑ የሪፎርም ተግባራት ተጨባጭ ስኬት እያስመዘገቡ ነው ብለዋል። 

በተቋም ደረጃ የተወሰዱ የሪፎርም እርምጃዎችም በአዳዲስ የለውጥ እሳቤ የሀገር ውስጥ ምርታማነትና የቴክኖሎጂ ሃሳቦችን የማፍለቅ አቅም እያሻሻለ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በሰው ሃብት ልማት የተፈጠረው አቅም አምራች ኢንዱስትሪው በእውቀትና ክህሎት የበለጸገ የሰው ሃይል እንዲያገኝ ማስቻሉን አንስተዋል።

በእውቀትና ክህሎት የበለጸገ የሰው ሃብት ለሥራ ኢንዱስትሪው ለማቅረብም በሰው ሰራሽ አስተውሎትና በሳይበር ቴክኖሎጂ የታገዘ ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትም በሰው ሃብት ልማት ላይ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት በመወጣት ትርጉም ያለው ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የተሰጡ የአጭር፣ መካከለኛና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎች ለሥራ ዕድል ፈጠራ ምቹ ምኅዳር መፍጠራቸውን አብራርተዋል።

በእውቀትና ክህሎት የበለጸገ የሰው ሃብት የማሰልጠን ተግባርም ከገበያ ፍላጎትና ጥራት ጋር የተጣጣመ የቴክኖሎጂ ሽግግር በመፍጠር አመርቂ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል።

በሥራ ዕድል ፈጠራ የተገኙ ስኬቶችም ዜጎች ከራሳቸው አልፎ ሃብትና ንብረት በማፍራት በሀገራቸው የኢኮኖሚ ዕድገት አሻራቸውን እንዲያሳርፉ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም