ቀጥታ፡

የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለን ከጥፋት መንገድ ተመልሰን መጥተናል - የቀድሞ ታጣቂዎች

ጎንደር፤ ህዳር 24/2018(ኢዜአ)፦ የህዝቡን የሰላም ጥያቄና የልማት ፍላጎት በመረዳት የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለን ከጥፋት መንገድ ተመልሰናል ሲሉ በአማራ ክልል የሰላምን ጥሪ ተቀብለው የመጡ የቀድሞ ታጣቂዎች ተናገሩ።

የቀድሞ ታጣቂዎቹ የሰላም ጥሪውን በመቀበል በዛሬው እለት በጎንደር ከተማ ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመኖር ገብተዋል።


 

ከቀድሞ ታጣቂዎቹ መካከል አበጀ ገላው፤ በተሳሳተ መንገድ ጫካ በመግባት በህዝብ ላይ ጥፋት መፈፀሙን አንስቶ በድርጊቱ በመፀፀት ሰርቶና አገልግሎ ለመካስ መዘጋጀቱን ተናግሯል።


 

ብዙዎቻችን ወደ ጫካ የገባነው የተሳሳተ አረዳድ ይዘን ነው ሲል ገልጾ አሁን ላይ እውነታውን በመገንዘብ ወደ ሰላማዊ ህይወት እየተመለስን እንገኛለን ብሏል።


 

በዚህም መሰረት እርሱና ሌሎች ጓደኞቹ የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ሰላማዊ ህይወት ለመምራት መምጣታቸውን አረጋግጧል።

የህዝቡን የሰላም ጥያቄና የልማት ፍላጎት በመረዳት ከጥፋት ወጥተን የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለን መጥተናል ብሏል።

የበደልኩትን ህዝብ በልማት በመካስ ከዚህ በኋላ ከተሳሳተ መንገድ እራሴን በማግለል አዲስ ህይወት ለመምራት ቁርጠኛ በመሆን የሰላም ጥሪውን ተቀብዬ ገብቻለሁ ሲሉም ገልጿል፡፡

ቁርጠኛ በመሆን የሰላም ጥሪውን ተቀብዬ ገብቻለሁ ብሏ


 

ሌላኛው የሰላምን መንገድ መርጦ የመጣው አማረ ምትኩ፤ በቆዩበት የተሳሳተ መንገድ ህዝብን ሰላም ከመንሳትም ባለፈ ብዙ በደሎችን ማድረሳችን እኔና መሰል ጓደኞቼን ጸጸት ላይ ጥሎናል ሲል ተናግሯል።

በመሆኑም ከጥፋት በመውጣት ለሰላምና ልማት ዝግጁ በመሆን ህዝባችንን በስራ ለመካስ መጥተናል በማለት ሌሎችም በተሳሳተ መንገድ የሚገኙ ሁሉ የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል እንዲመጡ መክሯል።


 

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መከላከል ምክትል መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ስማቸው አደመ፤ በከተማው በህብረተሰቡ ተሳትፎ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን መቻሉን ተናግረዋል።

በተሳሳተ መንገድ የባዳ ተልእኮ ፈፃሚ የነበሩና ህዝብን የበደሉ የቀድሞ ታጣቂዎች እየተመለሱና ሰላማዊ ህይወት እየመሩ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የቀድሞ ታጣቂዎቹን በማቋቋም ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ እየተደረገ መሆኑን አንስተው አሁን የመጡትም የተሃድሶ ስልጠና ወስደው በተመሳሳይ ሁኔታ ህይወታቸውን እንዲመሩ ይደረጋል ብለዋል።

ከቀናት በፊት የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ 15 የቀድሞ ታጣቂዎች በጎንደር ከተማ የሰላም አማራጭን በመቀበል ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመመለስ በመወሰን መግባታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም