ድርድርን በመግፋት የቅኝ ግዛት አስተሳሰብን ለማራመድ የሚደረገው የግብጽ እንቅስቃሴ ከወቅቱ እውነታ ጋር የማይሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ድርድርን በመግፋት የቅኝ ግዛት አስተሳሰብን ለማራመድ የሚደረገው የግብጽ እንቅስቃሴ ከወቅቱ እውነታ ጋር የማይሄድ ነው
አዲስ አበባ፤ሕዳር 24/2018(ኢዜአ)፦በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮችን በመግፋትና የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብን ለማራመድ የሚደረገው የግብጽ መንግስት ባለስልጣናት ተደጋጋሚ እንቅስቃሴ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን እውነታ ጋር የማይሄድ ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ የግብጽ መንግስት በአባይ ወንዝ ላይ የቅኝ ግዛት ዘመን የበላይነትን ለማስጠበቅ የሚያደርገው ተደጋጋሚ ጥረት ወቅቱን የማይመጥን ነው ሲል አውግዟል።
ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በትብብር ለመልማት ሁሌም ቁርጠኛ መሆኗን የገለጸው ሚኒስቴሩ የፓን አፍሪካ የረጅም ጊዜ አሻራ እና ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ የቆየ የቅኝ ግዛት እሳቤዎችን በፍጹም አትቀበልም ብሏል።
ፍትሃዊ፣ ምክንያታዊና እኩልነትን መሰረት ያደረገ የውሃ ሀብት አጠቃቀም የዓለም አቀፍ ሕግ ገዢ ጽንሰ ሀሳብ መሆኑን አመልክቶ ኢትዮጵያም ሀብቷን ለመጠቀም ከማንኛውም አካል ፍቃድ መጠየቅ አያስፈልጋትም ሲል ገልጿል።
መግለጫው ፤ግብጽ የሁለትዮሽ ድርድሩን ወደ ጎን በመተው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያ ላይ የምታሰራጨው መሰረት ቢስ ውንጀላ ተቀባይነት የለውም ብሏል።
ዓለም አቀፉ ማህረሰብ የግብጽን ጸብ አጫሪ ባህሪ እንዲያወግዝም ሚኒስቴሩ ጠይቋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶች የአፍሪካ ራስን መቻል የሚያሳዩ እንደሆኑም አመልክቷል።
ኢትዮጵያ ለትብብርና ሁሉንም ተጠቃሚ ለሚያደርጉ የመፍትሄ ሀሳቦች በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ነው በመግለጫው ላይ የተጠቀሰው።
ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን አሁን ላለውና ለቀጣይ ትውልዶች በመጠቀም መብቷ ጸንታ እንደምትቀጥልም ሚኒስቴሩ አስገንዝቧል።