ቀጥታ፡

በክልሉ የአርሶ አደሩን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተሰራው ስራ ውጤታማ ነው 

‎‎ሀዋሳ፤ ሕዳር 24/2018(ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትናና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ተናገሩ።

በክልሉ በመኸር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከለማው መሬት 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተመላክቷል።

‎የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በደቡባዊ ሲዳማ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በመኸር ወቅት የለማ ሰብልን ተመልክተዋል።

በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት፤ በክልሉ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትናና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ሥራዎች ውጤታማ ሆነዋል።


 

በመኸር ወቅት የለማ ሰብል በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ደስታ ይህም በምግብ ራስን ለማቻል፣ ገበያን ለማረጋጋትና ለኢንዱስትሪ ግብአት እንዲሆን የተቀመጠውን ግብ ማሳካት እንደሚያግዝ  አመላካች ነው ብለዋል።

ከዚህ በፊት ምርት የማይሰጡ መሬቶች ጭምር እንዲታረሱ የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂ አቅርቦትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱንም ጠቅሰዋል።

‎መኸር አብቃይ በሆኑ የክልሉ ደጋማ አካባቢዎች መሬቱ በአሲዳማነት የመጠቃት እድሉ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው አሲዳማ መሬትን በኖራ በማከም ምርታማነትን የማሳደግ ስራም በልዩ ትኩረት ተሰርቷል ብለዋል።


 

በመኸር ወቅት በክልሉ ከ117 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ እና ሌሎች ዋና ዋና ሰብሎች መልማቱን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ ናቸው።   

ከዚህም 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።


 

እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ ‎በክልሉ በመኸር ወቅት ከለማው አጠቃላይ መሬት 45 በመቶ የሚሆነው በኩታ ገጠም የለማ ነው።

በአሁኑ ወቅትም ምርትን በአግባቡ መሰብሰብ፣ የገበያ ትስስር መፍጠርና ለፋብሪካ ግብዓት ማቅረብ ትኩረት የተሰጣቸው መሆኑን አቶ መምሩ ጠቁመዋል።

ከአሰላ ብቅል ፋብሪካ ጋር በተፈጠረ የገበያ ትስስር ከ35 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን መሬት በቢራ ገብስ እንዲለማ ተደርጓል ብለዋል።

በዳራ ኦቲልቾ ወረዳ የአበራ ጌሌዴ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደጋጋ ሀጣላ፣ ስምንት አርሶ አደሮች በጋራ ሆነው በ12 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በኩታ ገጠም እያለሙ መሆናቸውን ገልፀዋል።


 

‎ከአምስት ዓመት በፊት የምርት ማሳደጊያ እና ዘመናዊ የግብርና አሰራር ባለመጠቀማቸው የሚያገኙት ምርት ከቤት ፍጆታ ያለፈ እንዳልነበርና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለገበያ ለማቅረብ ጭምር ተግተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በዚህም ከማሳቸው በሄክታር ከ40 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበስቡ አስረድተዋል፡፡


 

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ ምልከታ ያደረጉት በዞኑ ሁላ እና ዳራ ኦቲልቾ ወረዳዎች በኩታ ገጠም የለማ የመኸር ሰብልን ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም