ቀጥታ፡

ቀኑ በስኬት እንዲከበር ዝግጅት ተደርጓል

ሆሳዕና፤ ህዳር 24/2018(ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለሚከበረው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ስኬታማነት ማህበረሰቡንና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ያሳተፈ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው ለበዓሉ ስኬታማነት የተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች በማስመልከት ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በመግለጫው የቢሮው ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ እንዳሉት፣ 20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በስኬት እንዲከበር ከሰላምና ጸጥታ ጋር የተያያዙ ዝግጅቶች ተደርገዋል።

የዝግጅት ሥራው ማህበረሰቡን፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችንና የሰላምና ጸጥታ ተቋማትን ያሳተፈ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

በዓሉን ለማክበር እንግዶች ወደ ክልሉ መግባት እንደጀመሩ የጠቆሙት ሃላፊው የማረፊያና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ስፍራዎችን የማዘጋጀት  ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም የከተማው ነዋሪ የበዓሉ ታዳሚዎችን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ለሚከናወኑ ተግባራት ተባባሪ እንዲሆን አስገንዝበዋል።

በበዓሉ አከባበር ሂደት የሚያጋጥሙ ወንጀሎችን ፈጥኖ ለመፍታት ጊዜያዊ ችሎቶች መቋቋማቸውንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም