ኢትዮጵያ ስታትስቲክስ በልማት ዕቅድና ትግበራ ሂደት ስትራቴጂክ ሚና እንዲኖረው አድርጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ስታትስቲክስ በልማት ዕቅድና ትግበራ ሂደት ስትራቴጂክ ሚና እንዲኖረው አድርጋለች
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 24/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ብሔራዊ የስታትስቲክስ ልማት በልማት ዕቅዶችና በትግበራ ሂደት ስትራቴጂክ ሚና እንዲኖረው ማድረጓን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ(ዶ/ር) ገለጹ።
ዋና ዳይሬክተሩ ይህን ያሉት 19ኛው የአፍሪካ ስታትስቲክስ ተቋማት ዋና ዳይሬክተሮች ኮሚቴ ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ በተከፈተበት መርኃ ግብር ላይ ነው።
ኢትዮጵያ ለስታትስቲክስ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቷን በመግለፅ፥ በመተግበር ላይ ያለውን የሦስት ዓመት ብሔራዊ የስታትስቲክስ ልማት ፕሮግራም ለአብነት አንስተዋል።
በዚህም የስታትስቲክስ አቅምን የማጠናከር፣ የዳታን ወቅታዊነትና ጥራት የማሻሻል እንዲሁም የግብርና ቆጠራ እና የኢኮኖሚ ተቋማት ቆጠራን ጨምሮ ስትራቴጂክ ጥናቶች እየተካሄዱ ነው ብለዋል።
በመረጃ ላይ የተመሠረተ የፖሊሲ አወጣጥና ውሳኔ አሰጣጥን የሚደግፍ የተቀናጀና አስተማማኝ የስታትስቲክስ ሥርዓት እየተገነባ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህም ኢትዮጵያ የስታትስቲክስ አቅሟን ለማጠናከር ያላትን የማይናወጥ ቁርጠኝነት የሚያሳይና ስታትስቲክስን በልማት ዕቅድና ትግበራ ስትራቴጂካዊና ብሔራዊ ሚና እንዲኖረው ማድረጓን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የአፍሪካ ስታትስቲክስ ተቋማት ዋና ዳይሬክተሮች ኮሚቴ ሊቀመንበር ንያካሲ ሳንያንግ በበኩላቸው፥ የዳታ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ የስታትስቲክስ ባለሙያዎች ሚና ከመቼውም ጊዜ በላይ ወሳኝ ሆኗል ብለዋል።
በአህጉሪቱ የስታትስቲክስ ስምምነቶችንና የተቋቋሙ የቴክኒክ ቡድኖችን በተሟላ ሁኔታ ወደ ተግባር ማስገባት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዚህ ዘመን ዳታ ከመረጃነት ባለፈ የልማት አንቀሳቃሽ ኃይል በመሆኑ ጥራት ላለው ስታትስቲክስ በቅንጅት መትጋት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የአፍሪካ ስታትስቲክስ ማዕከል ዳይሬክተር ሳሙኤል ኮቢና፥ ስታትስቲክስ የአፍሪካን የልማት ችግሮች ለመፍታት ዋነኛው መሣሪያ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በአስደማሚ የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኑን ጠቅሰው፥ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት አድንቀዋል።
የስታትስቲክስ ማኅበረሰቡ ከቁጥር ባለፈ የአፍሪካውያንን መጻኢ እጣ ፋንታ የተሻለ የሚያደርጉና በትክክል የሚያመላክቱ መረጃዎችን ማመንጨት አለበት ብለዋል።
በተለይም መንግሥታት የሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች በመጪው ትውልድ ላይ የሚኖራቸውን ተጽዕኖ ታሳቢ እንዲያደርጉ ትክክለኛ መረጃዎችን በማቅረብ ማገዝ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ማኅበራዊ አመልካቾች ከኢኮኖሚ አመልካቾች ጋር ያላቸውን ጠንካራ ትስስር በማሳየት ማንም ከዕድገትና ከልማት ወደ ኋላ እንዳይቀር ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የአፍሪካ ስታትስቲክስ ማዕከል ከዓለም አቀፉ የስታትስቲክስ ተቋም ጋር በመተባበር ለአባል ሀገራት የሚያደርገውን ድጋፍና ስትራቴጂያዊ አጋርነት እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።