ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ አረንጓዴ ፋይናንስን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ እንዲሆን በምታደርገው ጥረት የካፒታል ገበያ ቁልፍ ሚና አለው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 24/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ፋይናንስን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ እንዲሆን በምታደርገው ጥረት የካፒታል ገበያ ቁልፍ ሚና እንዳለው የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሀጽዮን ገለጹ፡፡

በአዲስ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል እየተካሄደ ያለው ሁለተኛው ቀጣናዊ የካፒታል ገበያ ስብሰባ ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሀጽዮን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማት መገንባት የሚየስችል ጥረት እያደረገች ነው፡፡

ኢትዮጵያ የዜጎች ብልጽግና መሰረት የሚጥል የአረንጓዴ ሥነ ምህዳር ለመፍጠር በርካታ ተግባራትን ማከናወኗን ገልጸዋል፡፡

በአረንጓዴ ፋይናንስ ስርዓት በትራንስፖርት፣ በግብርና፣ በኢነርጂ፣ በኢንዱስትሪና ከተማ መሰረተ ልማት የካርበን ልቀትን መቀነስ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም በአረንጓዴ ፋይናንስ እና በካፒታል ገበያ መካከል ትስስር በመፍጠር የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ መመሥረት እንደ ሀገር አዲስ የፋይናንስ ዝማኔን እንደሚፈጥር በመግለጽ፤ ይሄውም ከብሔራዊ የትኩረት አጀንዳዎች ጋር የተያያዘ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ አይበገሬነትን፣ ዘላቂነት እና የኢኮኖሚ ሽግግርን ብሔራዊ የትስስር አጀንዳ በማድረግ የአየር ንብረት ፖሊሲን መተግበር የሚያስችሉ ተግባራትን እውን ማድረጓን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ተወዳዳሪነትን፣ ሥራ ፈጣሪና ፈጣን ዕድገትን በማስመዝገብ ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ዕድገት ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ፋይናንስ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ እንዲሆን በምታደርገው ጥረት የካፒታል ገበያ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ገልጸው፤ መንግሥት የተቋማትን የቁጥጥር ስርዓት በማጠናከር የፋይናንስ ዘርፉን እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ የኢኮኖሚ ሽግግሩን በማሳለጥ ዘላቂ ዕድገት ማረጋገጠ የሚያስችል ቁልፍ መሳሪያ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማት ግቦች እውን ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ አጋር አካላት፣ ባለሃብቶችና የዘርፉ ተዋንያን በትብብር መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም