ቀጥታ፡

ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የበኩላችንን እንወጣለን - የኃይማኖት አባቶች

ደሴ ፤ ህዳር 24/2018(ኢዜአ)፦የመከባበርና የአብሮነት እሴቶችን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።

የደሴ ከተማ አስተዳደርና የደቡብ ወሎ ዞን የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ "ሐይማኖቶች ለሰላም፣ ለአብሮነትና ለመከባበር" በሚል መሪ ሃሳብ ውይይት እየተካሄደ ነው።


 

በደሴ ከተማ እየተካሄደ ባለው መድረክ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባልና የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ቦርድ አባል ሸህ እንድሪስ አሊ፣ ሁሉም ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት አንስተዋል።

 ሰላም እንዲጸና በእምነት ተቋማት የሰላምን ዋጋ አበክረን ማስተማር ይኖርብናል ብለዋል።


 

የደቡብ ወሎ ዞን ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢና የዞኑ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ቆሞስ አባ ለይኩን ወንድይፍራው ፤ ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናት በቅንጅት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ሕብረተሰቡ የሰላም ባለቤትነቱን በተግባር እንዲያፀና እንደ ሀይማኖት አባት የሰላምን ዋጋ በማስገንዘብ ሚናቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።   

የመከባበር፣ የአብሮነትና የመተጋገዝ ባህልን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም  ቆሞስ አባ ለይኩን አንስተዋል።


 

የደሴ ከተማ አስተዳደር ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢና የደሴ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸህ ሀሰን ሀሚዲን በበኩላቸው እንዳሉት፤ የሁሉም እምነቶች አስተምህሮ ሰላምና አንድነትን መሰረት ያደረገ ነው።ሁሌም ስለሰላም አስፈላጊነት በማስተማር የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።

ዘላቂ ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት ነው ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባልና የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ማዕከላዊ ሰሜን ኢትዮጵያ ሲኖዶስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዋኘው አንዳርጌ ናቸው።

የአካባቢው ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመደገፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የሕዝብን ሰላም በመንሳት ግፍና በደል የሚፈጽሙ የጥፋት ተላላኪዎችን በጋራ በቃችሁ ልንላቸው ይገባል ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን ናቸው። 


 

የሐይማኖት አባቶች አጥፊዎችን በመምከር፣ በማስተማርና በመገሰፅ የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ በማድረግ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።  

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፤ ለከተማው ዘላቂ ሰላምና ልማት መጠናከር ሁሉም ሀላፊነት አለበት ብለዋል።


 

በተለይ የሀይማኖት አባቶች ምዕመናን በማስተማርና በመምከር ሰላም፣ አብሮነትና ልማትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ቀጣይነት ያለው ሥራ መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረክ ከፌዴራል፣ ከክልል፣ ደቡብ ወሎ ዞን እና የደሴ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ የሀይማኖት አባቶች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም