በክልሉ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤት እየታየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤት እየታየ ነው
ባህር ዳር ፤ ሕዳር 24/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ ረገድ አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የክልሉ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ገለጸ።
“አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማህበረሰብ መገንባት ለተሻለ ማህበራዊ እድገት” በሚል መሪ ሃሳብ የአካል ጉዳተኞች ቀን በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ተከብሯል።
የክልሉ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ፍሬሰላም ዘገየ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በክልሉ የአካል ጉዳተኞችን መብት በማስጠበቅና ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ረገድ አበረታች ለውጦች እየታዩ ነው።
በክልሉ የሚኖሩ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነታት ለማረጋገጥ አደረጃጀቶች ተፈጥረው እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የአካል ጉዳተኞችን መብት በማስከበር ረገድ ብዙ መሻሻሎች እንዳሉ ጠቁመው አሁን ላይ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ንጹህ ሽፈራው በበኩላቸው እንዳሉት፤ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የበለጠ ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው።
አካል ጉዳተኞችን አካታች የሆነ የፖለቲካ፣ የልማትና የኢኮኖሚ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፤ አሁንም በአመለካከት ደረጃ ያልተፈቱ ችግሮች መኖራቸውንና ለዚህም በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።
አካል ጉዳተኞች በሚችሉት አቅም ሁሉ ሰርተው ራሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን መጥቀም እንዲችሉ የቅንጅት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉም አረጋግጠዋል።
በባህር ዳር ከተማ አካል ጉዳተኞች በሚፈጠሩ የስራ እድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሰብለ ዘውዱ ናቸው።
አካል ጉዳተኞች መብታቸውን በማስከበር ራሳቸውንና ሌሎችን የመጥቀም እምቅ አቅማቸውን በስራ ላይ እንዲያውሉ ለማድረግ የክትትልና ድጋፍ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመድረኩ የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ የዘርፉ አመራሮችና የአካል ጉዳተኞች ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።