ድጋፉ የጤና አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ያግዛል - ኢዜአ አማርኛ
ድጋፉ የጤና አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ያግዛል
ሰመራ፤ ሕዳር 24/2018(ኢዜአ)፦ ለአፋር ክልል ጤና ቢሮ የተደረገው የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ የጤና አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ያግዛል ሲሉ የቢሮው ሃላፊ አቶ ያሲን ሃቢብ ተናገሩ።
በካናዳ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ያሰባሰቡትን የህክምና መሳሪያዎች በተወካያቸው አማካኝነት ለአፋር ክልል ጤና ቢሮ አስረክበዋል።
ድጋፉ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የወጣበት መሆኑም ተመላክቷል።
በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አቶ ያሲን ሃቢብ እንዳሉት፤ ቢሮው በጎ ፈቃደኞችን እና አጋዥ አካላትን በማስተባበር የጤና አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል።
ዛሬ የተደረገው ድጋፍም በክልሉ በሚገኙ የጤና ተቋማት የጤና አገልግሎት አሰጣጡን በእጅጉ የሚያግዝና የአቅርቦት ዕጥረትን የሚያቃልል ነው ብለዋል።
ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት አቶ ያሲን፤ ሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶችና በጎ አድራጊዎችም ይኸንን አርአያ ተከትለው መሰል ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ድጋፉን ያስረከቡት የበጎ ፈቃደኞቹ ተወካይ ወይዘሮ ብርትኳን ካሳ በበኩላቸው፤ ወገን ለወገን የሚያደርገው ድጋፍ በእኛ በኢትዮጵያዊያን የነበረና አሁንም ያለ መልካም ባህላችን ነው ብለዋል።
በካናዳ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በትብብር በመሆን የሚያደርጉት እገዛ በዚህ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው መሆኑን ገልፀዋል።
በድጋፍ ከተበረከቱ የህክምና መሳሪያዎች መካከል ዘመናዊ የህሙማን አልጋዎች፣ ማሞቂያዎች፣ ዊልቸር፣ ስትሬቸር፣ ክራንች እንዲሁም ኮምፒውተሮች ይገኙበታል።