ቀጥታ፡

በአረንጓዴ ልምላሜ ያጌጠው - የቤንቾች ቀዬ

በአረንጓዴ ልምላሜ ያጌጠው - የቤንቾች ቀዬ

(በቀደሰ ተክሌ) -ከሚዛን ቅርንጫፍ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሚገኘው የቤንች ምድር የሰጡትን የሚያበቅል ክረምት ከበጋ የማይጠወልግ ልምላሜን የታደለ ክልል ነው። 

በቤንች ሸኮ ዞን ባሉ የተለያዩ ወረዳዎች ደን የሚመስልና በመኖሪያ መንደሮች የሚታየው አብዛኛው አረንጓዴ ስፍራ ለምግብነት የሚያገለግሉ ፍራፍሬዎች፣ ቅጠሎችና ስሮችን የያዘ ነው። 

የቤንቾች ቤት ዙሪያው በአረንጓዴ ተፈጥሮ ያጌጠ ነው። የቤታቸው ሞገስ፤ የምግብ ዋስትናቸውም ጭምር ነው። ከዚህ ከፍ ሲል ደግሞ ቤንቾች ነፋሻማ አየር እየማጉ የመኖር ልምድን ያጎናጸፋቸው ይኸው አፈር ቆፍረው ዘር ተክለው ያበቀሉትና የተንከባከቡት አረንጓዴ ሀብት ነው። 

ከአንድ አርሶ አደር ማሳ እንሰት፣ ሙዝ፣ ጎደሬ፣ ፓፓያ፣ አቮካዶ፣ ብርቱካን እና ሌሎች ፍራፍሬዎች ማየት የተለመደ ነው።


 

እግር ጥሎት ወደ ቀዬያቸው ያመራ እንግዳ ከፍራፍሬዎቹ የደረሰ ካለ ተቆርጦ ይሰጠዋል። በተጨማሪም ከብቶች፣ በጎችና ዶሮዎች የገቢ ምንጮቻቸው ናቸው። ወደ ቤታቸው ዘልቆ የገባ ሰው "ኪዥ" የተሰኘና የቤንች እናቶች ከወተት የሚያዘጋጁትን ''ጎደሬ'' ተብሎ ከሚጠራ የስራ ስር ምግብ ጋር ያጣጥማል። 

ቤንቾች በቆሎ፣ ማሽላ፣ ስንዴ፣ ባቄላ እንዲሁም ሌሎች የሰብል ዓይነቶችን ያለማሉ። ማር፣ ቡና፣ ኮረሪማ እና ሌሎች የተፈጥሮ ቅመማ ቅመሞችም ቤንቾች ከገበያ ገዝተው የሚያመጡት ሳይሆን ከማሳቸው የሚያፈሩት ነው።

የተቀናጀ እርሻን ባህል ያደረጉት ብርቱ የቤንች አርሶ አደሮች ወደ ገበያ አውጥተው የሚሸጡት እንጂ የሚገዙት የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። 

የፋብሪካ ውጤቶችን ለመግዛትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግም ከጓዳቸው ሞልቶ የተረፈውን ወደ ገበያ አውጥተው በመሸጥ ገበያን ያረጋጋሉ።

በጠንካራ የእርሻ ባህላቸውም ምክንያት ልጆቻቸው የበሰለ ምግብን ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ፍራፍሬዎችንም ከጓሮና ከጫካ ቆርጠው ስለሚመገቡ ረሀብን አያውቁም።


 

የቤንቾች ቤት ዙሪያ ውብና ጽዱ ነው። ለዚህ ደግሞ ሴቶቹ የቤታቸውን ግድግዳ በተፈጥሮ ቀለም ከማስዋብ ጀምሮ ይጠበቡበታል። በቤንቾች ዘንድ የአንድ አርሶ አደር ጉብዝና የሚለካው በቤቱ ነው። ይህም የቤቱ ዙሪያ ያለው ውበትና የቤቱ ጥንካሬ ብቻም ሳይሆን ገላጣ መሆን አለመሆኑም ጭምር ከግምት ውስጥ ይገባል።

አባዎራው በማሳው ላይ የሰብል ስራውን ያከናውናል። ልጆችና እማውራዋ ደግሞ ይኮተኩታሉ ያርማሉ። ከዚህም በተጨማሪ የቤንች እናት ጎደሬና ሌሎች የጓሮ አትክልቶችን የማልማት ኃላፊነት አለባት። የቤታቸው ዙሪያና ቀዬው በሙሉ በአረንጓዴ ልምላሜ አጊጦ የሚታይበት ምስጢሩ ይሄው ነው። ከርቀት ደን መስሎ የሚታየው አረንጓዴው ቀዬአቸው የገቢ ምንጭም በመሆኑ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ነውም ማለት ይቻላል። 

የሌማት ትሩፋት እሳቤ ቀድሞ የገባቸው ቤንቾች ማር አይገዙም፤ ለእንቁላል ሸመታም ገበያ አይወጡም። ወተት ቢያምራቸው በትኩሱ፤ ከዛም አለፍ ሲል በባህላዊ መንገድ እርሾ ጨምረው የሚያዘጋጁት "ኪዥ" የተሰኘ የወተት ውጤትን እንደ አይብም እንደ እርጎም አደርገው ይጠቀሙታል።

የትኛውንም መልክዓ ምድር በሚስማማው የሰብል ዓይነት መሸፈን ያውቁበታል። መሬቱ ረግረጋማ ከሆነ ለጎደሬ፤ ዳገታማ ሆኖ ለማረስ የሚያስቸግር ከሆነ ደግሞ ለሙዝ ልማት ያውሉታል። 


 

የምግብ ዋስትናን በቤተሰብ ደረጃ ለማረጋገጥ ሥራ የሚሠራው በጓሮ ነው። ይህም ሁሉን ከአንድ ጓሮ ለማግኘት በመጣር የሚመጣ ነው። ይህም ካልሆነ ደግሞ አስተማማኝና ቋሚ ምርት ማሳ ላይ አልያም ጎተራው ላይ ማኖር ያስፈልጋል። 

እንደ ቤንቾች በቤተሰብ ደረጃ ምግብን በራስ አቅም ለመቻል የሚደረገው ጥረት እንደሀገር ሲጠናከር ለውጡ ቀጣይነት ባለው መልኩ ይፋጠናን።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ቁጥር አብዛኛው አርሶ አደር ነው። ይሁን እንጂ ጾሙን የሚያድር ሰፊ መሬት እንዳለ መረጃዎች ያመለከታሉ። አንድም መሬት ጾም እንዳያድር በየአካባቢው ስራዎች ቢጀመረም ውጤቱ ቀሪ ሥራዎችን የሚጠይቅ ነው። ዛሬም በምርት እጥረት የኑሮ ውድነትና መሰል ችግሮች ይስተዋላሉ። በእነዚህ መሬቶች ላይ ሰርቶ ከመለወጥ ይልቅ ከተማ ቁጭ ማለትን የሚሻ ትውልድ ማየት የተለመደ ነው።  

የቤንች ሸኮ ዞን አርሶ አደሮች እጃቸው ብርቱ በመሆኑ እነዚህ ችግሮች በስራ አሽንፈዋል። ይህም በምግብ ራሳቸውን ከመቻል ባለፈ በኢኮኖሚም እንዲረጋጉ አድርጓቸዋል። 


 

ለሀብት ምንጭ የሆነን ማሳ ለቆ ከተማ በመዋል የሚገኝ ነገር አይኖርም። በከተማም ሆነ በገጠር ለመለወጥ እንደ ቤንቾች ብርቱ እጆች ያስፈልጋሉ። ካልተሰራ ገቢ ሳይሆን ወጪ እያደገ ወዳልተገባ መንገድ ለመሄድ ምክንያት ይሆናል። ለችግርም ሆነ ሰርቶ የመለወጥ ዕድሉ የሚወሰነው በምርጫችንና ለሥራችን በምንሰጠው ትኩረት ነው። 

እንደ ቤንች ሸኮ ዞን አርሶ አደሮች ሰርቶ ለመለወጥና ራስን ለመቻል በየአካባቢው ያለን የተፈጥሮ ሀብት ወደ ልማት ለመቀየር ተግቶ መስራት ያስፈልጋል ። ሰላም!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም