ያሉንን ሃብቶች በማልማት ህብረተሰባችንን ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንሰራለን - ኢዜአ አማርኛ
ያሉንን ሃብቶች በማልማት ህብረተሰባችንን ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንሰራለን
ሰመራ ፤ ህዳር 24/2018(ኢዜአ)፦ ያሉንን ሃብቶች በመጠቀምና በማልማት ህብረተሰባችንን ተጠቃሚ ለማድረግ ተዘጋጅተናል ሲሉ የአፋር ክልል ሰልጣኝ አመራሮች ተናገሩ።
በክልሉ “በመደመር መንግስት ዕይታ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሀሳብ ለመካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በስልጠናው ማጠቃለያ በሰጡት ማብራሪያ ላይ ፤ መፍጠር፣ መፍጠን፣ ማብዛት እና ማጥራት ላይ ትኩረት በማድረግ ለውጤታማነት መስራት እንደሚገባ መናገራቸው ይታወሳል።
በአፋር ክልል ኢዜአ ያነጋገራቸው የስልጠናው ተሳታፊ አመራሮች እንደገለጹት፤ በስልጠናው ያገኙትን እውቀት ከክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ለክልሉ ህዝብ ተጠቃሚነት በቁርጠኝነት ይሰራሉ።
ከአመራሮቹ መካከል የቡሩሞዳይቱ ወረዳ አስተዳደሪ አቶ መሐመድ ሐሰን፤ በወረዳው የሚገኘው ሐይቅና ሌሎች ሀብቶች ላይ ወጣቶችን አደራጅቶ ወደስራ ለማስገባት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
በቀጣይም የቱሪዝም ሀብቶችን እና ሌሎችን በማልማት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።
በወረዳው ባሉ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች የተለያዩ የግብርና ልማት ሥራዎችን በመስራት ተጠቃሚነት ማሳደግ ላይ በፍጥነትና በጥራት ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሰሙሮቢ ወረዳ ሲቪል ሰርቪስ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አይትሌ ማቴ በበኩላቸው ፤ መሬት፣ ውሃና የሰው ጉልበት እያለ የእርሻ መሬቶችን ጦም ላለማሳደር ተግተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡን በማሳተፍ ውጤታማ ሥራ ለመስራት ዝግጁ ነን ያሉት አመራሩ፤ በተለይም የተሰጠንን ኃላፊነት ተገንዝበን ምርታማነትን በማሳደግ ተረጂነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ስራዎችን እንሰራለን ብለዋል።ለስኬታማነቱም እስከ ታች ድረስ ያሉ መዋቅሮችን በመጠቀም እንደሚሰራ ነው የገለጹት።
የተላላክ ወረዳ ትምህርት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በርኦ ዓሊ በበኩላቸው፤ በወረዳው ያሉትን አቅሞችና ሀብቶች አውቀን ወደልማት ለመቀየር ተዘጋጅተናል በማለት ተናግረዋል።