ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እንዲጠናከር እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እንዲጠናከር እየሰራ ነው
መቀሌ፤ህዳር 24/ 2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ በምክክር ሂደቱ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እንዲጠናከር እየሰራ መሆኑን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።
ዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች ቀን “አካል ጉዳተኞችን የሚያካትት ማህበረሰብ መገንባት ለተሻለ ማህበራዊ እድገት" በሚል መሪ ሃሳብ በመቀሌ ከተማ ተከብሯል።
በመድረኩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በምክክር ሂደቱ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ሚና እንዲጠናከር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በእስካሁኑ የምክክር ሂደትም በተለይም አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶችንና ወጣቶች በንቃት እንዲሳተፉ ስለመደረጉ አንስተው፥ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ ዓሊ በበኩላቸው፥ የአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት የፖሊሲ ማሻሻያ ጭምር በማድረግ የአካል ጉዳተኞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አንስተዋል።
በመንግስት አስተዳደር በውሳኔ ሰጪነት ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርጉ፣ መብትና ጥቅሞቻቸው እንዲከበሩ እንዲሁም የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በማህበራዊ አገልግሎት በተለይም በትምህርትና ሌሎችም ዘርፎች ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፥ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ፤የአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች ቀን ሲከበር ለሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው ይበልጥ ለመስራት በመዘጋጀት መሆን አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሂዳያ አሊ፤ ለአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ተጠቃሚነት በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት መልካም ጅምሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
እለቱ ሲከበርም የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጠናከር ብሎም በማህበረሰቡ ዘንድ ክብርና እንክብካቤ እንዳይለያቸው በማስገንዘብ መሆኑን ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች ቀን በኢትዮጵያ ዘንድሮ ለ34ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።