የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የአካባቢያቸው ሰላም ፀንቶ እንዲቀጥል ሚናቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የአካባቢያቸው ሰላም ፀንቶ እንዲቀጥል ሚናቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል
ጎንደር፤ ሕዳር 24/2018(ኢዜአ)፡- ተሰሚነታቸውን በመጠቀም የአካባቢያቸው ሰላም ፀንቶ እንዲቀጥል ሕብረተሰቡን በማስተባበር ሚናቸውን ይበልጥ እንደሚያጠናክሩ የጎንደር ከተማና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።
የጎንደር ከተማና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰላም እሴት ግንባታ ዙሪያ ያዘጋጁት ሕዝባዊ የሰላም ጉባኤ ዛሬ ተካሄዷል፡፡
የጉባኤው ተሳታፊ መላእከ ገነት ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል ደርበው እንደገለፁት፤ ሠላም በጋራ ጥረትና ርብርብ የሚረጋገጥ በመሆኑ ለሠላም ግንባታ በሚደረገው ጥረት ተሳትፎአችንን አጠናክረን እንቀጥላለን።
ሰላም የሃይማኖቶች ሁሉ መሠረትና እምነት በመሆኑ ታላቅና ቀዳሚ ተልእኳችን በማድረግ ለሃይማኖታዊ አስተምህሮ ትኩረት ሰጥተን ህዝባችንን ለማገልገል ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
የሀገር ሽማግሌ አቶ ገብሬ ሞገስ በበኩላቸው፤ በተሳሳተ መንገድ ጫካ የገቡ ታጣቂዎች ከድርጊታቸው ተጸጽተው ወደ ሠላም እንዲመጡ በማድረግ በኩል የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የትጥቅ ትግል እርስ በርስ ከመጎዳዳት ውጪ ሠላምና ልማትን የሚያረጋግጥ ባለመሆኑ የሽምግልና እሴቶቻችንን ተጠቅመን ታጣቂዎች የሠላምን አማራጭ ተቀብለው ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ የበኩሌን እወጣለሁ ብለዋል፡፡
ታጣቂዎች ሠላምን ምርጫ አድርገው እድሉን ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ያሳሰቡት ደግሞ አቶ አስረስ መሃመድ ናቸው።
እኛ የሀገር ሽማግሌዎች ከቀደሙ አባቶቻችን የተቀበልነው ዘመን ተሻጋሪ የሽምግልና እሴቶች ያሉን በመሆኑ ለእርቅ ለፍቅርና ለአንድነት በመጠቀም ሰላምን ለማጽናት ተግተን እንሰራለን ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ አባል የሆኑት መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል በበኩላቸው፤ ብዝሃ ሃይማኖትን ባከበረ መልኩ ለሰላም ለፍቅርና ለእርቅ በጋራ መቆም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ትልቁ ተልእኳችን ሰላም ነው ያሉት መምህር ዳንኤል የሃይማኖት ተቋማት ሰላምን የመገንባት ትልቅ አቅም ያለን በመሆኑ ስለ ሰላም አጥብቀን ልንሰራ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የጎንደር ከተማ ኡለማዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሀጂ ኢብራሂም መሃመድ በበኩላቸው፤ ሃይማኖታዊ አስተምህሮን መሰረት በማድረግ የእምነቱ ተከታዮች ለሰላም አጥብቀው እንዲሰሩ የዘወትር ጥረት እንዳርጋለን ብለዋል፡፡
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፤ አሁን ላይ በከተማው ለሰፈነው አስተማማኝ ሰላም የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ድርሻ የላቀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሰላም በመንግስት ጥረት ብቻ የሚረጋገጥ ባለመሆኑ በከተማው ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለፍጻሜ እንዲበቁ በማድረግ በኩል የሃይማኖት ተቋማትና የሀገር ሽማግሌዎች ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡
በህዝባዊ የሰላም ጉባኤው ላይ ከጎንደር ከተማና ከማእከላዊ ጎንደር ዞን የተውጣጡ የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦችና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል፡፡