ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት ታሪክን እንደትምህርት በመውሰድ ታሪክ ሰሪ የሆነ እሳቤን ይከተላል

አዲስ አበባ፤ሕዳር 24/2018 (ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት ታሪክን እንደትምህርት በመውሰድ ታሪክ ሰሪ የሆነን እሳቤን እንደሚከተል የታሪክ ምሁሩ ታምራት ሃይሌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የመደመር መንግሥት የታሪክ አረዳድ በኢትዮጵያ ትናንት፣ ዛሬና ነገ መካከል ባለው አሰባሳቢና አስተሳሳሪ ዕይታ የተመሠረተ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሃሳብ ለቀናት ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባላት የማጠቃለያ ስልጠና መስጠታቸው ይታወሳል።

በወቅቱም የመደመር መንግሥት የሚያሻግር ሃሳብ፣የሚሻገር ህዝብ ይዞ ለለውጥ የሚተጋ ስርዓት በመያዝ ታሪክን ከማውራት ይልቅ ታሪክን በመስራት እራሱን መግለጥ የሚሻ መሆኑን ገልጸዋል።

የታሪክ ምሁሩ ታምራት ሃይሌ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሰው ልጆች ታሪክ አረዳድ በግለሰብ፣ በማህበረሰብ፣ በሀገረ መንግስትና ዓለም አቀፍ ደረጃ የተወሰነ መሆኑን ገልጸዋል።

ታሪክም በዜጎች የትናንትና ዛሬ ማንነት እንዲሁም ከፖለቲካ ሥልጣንና አስተዳደር ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን ጠቁመዋል።

በ1950 በተጀመረ የኢትዮጵያ ዘመናዊ የታሪክ አስተምህሮም በመልካምና በተግዳሮት የታጀበ ቢሆንም፤ ታሪክን በነጣጣይና ቆሞ ቀር ትርክትነት የሚጠቀሙ የፖለቲካ ኃይሎች ሀገርን ዋጋ ማስከፈላቸውን አስረድተዋል።

የመደመር መንግሥት በታሪክ እሳቤ ላይ ያለው አተያይም በኢትዮጵያ ትናንት፣ ዛሬና ነገ መካከል ያለውን ሚዛን በልኩ በማየት የተመሰረተ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የመደመር መንግሥት የታሪክ ዕይታ ያለፉ ጥንካሬና ክፍተቶችን ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ አመላካች እሳቤ ማስቀመጡን አብራርተዋል።

በዚህም የመደመር መንግሥት በኢትዮጵያ ትናንት፣ ዛሬና ነገ መካከል ጥልቅ ትስስር መኖሩን የሚያመላክት እሳቤ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ካላት የታሪክ ሃብት አኳያ የምትገኝበት ሁኔታ የሚመጥነን አይደለም ያሉት ምሁሩ፤ በዚህም የመደመር መንግሥት ታሪክን እንደ ትምህርት በመውሰድ ታሪክ ሰሪ የሆነ እሳቤን የመዘርጋት አካሄድ ይከተላል ብለዋል።

በአጠቃላይ የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያ ታሪክ በትናንት፣ ዛሬና ነገ ትስስርና ቅብብሎሽ የሚሰራ እንደሚረዳ አብራርተዋል።

የመደመር መንግሥት ቀደም ካሉት የዘውዳዊ፣ የደርግ፣ የኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ሥርዓቶች ጋር ሲነፃጸር ለየት ያለ አዲስ ሀገር በቀል ዕይታን እንደሚከተል አስረድተዋል።

በዚህም የመደመር መንግሥት ሥርዓትም ትናንትን ከዛሬና ከነገ ጋር ተደማሪ በማድረግ የኢትዮጵያን የታሪክ ውስንነቶች እየፈታ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በዚህም ቀደምት የኢትዮጵያ የመንግስት አስተዳደር ስርዓቶች የትናንትን ታሪክ ያዩበት የነበረውን የአረዳድ ውስንነቶችን በማረም የመደመር መንግሥት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የመደመር መንግሥት የታሪክ ዕይታም ከቀደምት የኢትዮጵያ መንግስታት አኳያ አዲስ ዕይታን በማምጣት ሚዛኑን ለጠበቀ አሰባሳቢ ትርክት ግንባታ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል።

የመደመር መንግሥት የታሪክ አረዳድም አሰባሳቢና አስተሳሳሪ ዕይታ ያለው መሆኑን አንስተዋል።

ታሪክንም የአንድ ወገን ብቻ አድርጎ ባለመመልከት በስፋትና በጥልቀት፤ በዘመንና ሁኔታ፣ በባህልና ሃይማኖት የሁሉም መሆኑን የሚያትት አሰባሳቢ ዕይታ እንዳለው አንስተዋል።

በመደመር መንግሥት መጽሐፍም የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮች ኢትዮጵያ ያሉባትን ስብራት ታሪካዊ ዳራ በሚገባ የተረዳ እንደሆነም አስረድተዋል።

ከቀደሙት የኢትዮጵያ መንግስታት ርዕዮተ ዓለምም ሆነ ፖሊሲዎችና አስተዳደራዊ አቅጣጫዎች ከውጭ የሚቀዱ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህ ረገድ የመደመር መንግሥት እራስን በመመርመር ሀገር በቀል እሳቤን በማስቀመጥ ወደ ተግባር መግባቱን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም