የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ህብረ ብሔራዊ አንድነትን እያጎለበተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ህብረ ብሔራዊ አንድነትን እያጎለበተ ነው
ሐረማያ፤ ህዳር 24/2018 (ኢዜአ)፦ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ከፋፋይ ትርክቶችን በማስቀረት ህብረ ብሔራዊ አንድነትን እያጎለበተ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ተናገሩ።
ኢትዮጵያ የብዝኃ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክና እምነቶች መገኛ ሀገር ናት፤ ብዝኃ ማንነት፣ ባህል፣ ታሪክና እምነት ያላቸው ብሔረሰቦች ተዋደውና ተቻችለው በፍቅር የሚኖሩባት የሕብረ-ብሔራዊነት ተምሳሌት አገር ናት።
በዚህም 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርኃ ግብሮች በመከበር ላይ ነው።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ መሀመድ ሐሰን(ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነት እያጎለበተ መጥቷል።
በተለይ እለቱ በአብሮነት መከበሩ ከፋፋይ ትርክቶችን በማስቀረት ህብረ ብሔራዊ አንድነትን እያጎለበተ መምጣቱንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በታሪክ ውስጥ ባህልና ቋንቋን ተጋርተዋል፣ እሴቶቻቸውንም አጎልብተዋልያሉት ዶክተር መሀመድ፤ በዚህም የጋራ እድልና እጣ ፈንታ አላቸው ብለዋል።
ይህም በኢትዮጵያ የብሔሮች ብሔረሰቦና ህዝቦች ዘንድ ከፋፋይ ትርክት ቦታ እንደሌለው ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።
በተለይም በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተለያዩ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነትና ሌሎች እንዳሏቸውና በልዩነታቸው ውስጥ በጋራ አብረው እንደሚኖሩ የሚያሳዩበት በዓል ነው ብለዋል።
በዓሉ አብሮነትና የቆየ ትስስርን እያጎለበተና ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት እያስቻለ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ምሁራንም በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነትና ውበት የማጎልበትና ጠንካራ አገረ መንግስት የመገንባት ስራውን በጠንካራ መሰረት ላይ የማሳረፍ ስራ ላይ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባቸውና ይህም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።