ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስትተገብር ስታትስቲክስን ወሳኝ አምድ አድርጋለች - ሚኒስትር አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስትተገብር ስታትስቲክስን ወሳኝ አምድ አድርጋለች - ሚኒስትር አህመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 24/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአስር ዓመት መሪ የልማት እቅዱንና ሁለተኛውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስትተገብር ስታትስቲክስን ወሳኝ አምድ አድርጋለች ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።
አቶ አህመድ ሽዴ በአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደው 19ኛው የብሔራዊ ስታትስቲክስ ዋና ዳይሬክተሮች ኮሚቴ ስብሰባ ባደረጉት ንግግር፥ ኢትዮጵያ የስታትስቲክስ ስርዓቷን ለማዘመን እየሰራች ነው ብለዋል።
ስታትስቲክስ ለሀገራዊና አህጉራዊ የልማት አጀንዳዎች ስኬት ወሳኝ ሚና እንዳለው በማንሳት መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ለጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ዋነኛ አቅም መሆኑን ጠቅሰዋል።
ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ከሌለ አንድ ሀገር ውጤታማ የልማት ስትራቴጂዎችን መንደፍም ሆነ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ አይችልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአስር ዓመት የልማት ዕቅዷና የሀገራዊ ሪፎርም ዋነኛ አጀንዳ የሆነውን ሁለተኛውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መተግበር ስትጀምር ስታትስቲክስን ወሳኝ አምድ ማድረጓን ጠቅሰዋል።
የብሔራዊ ስታትስቲክስ አቅምን ማጠናከር፣ የመረጃ ጥራትን ማሻሻል እና ስታትስቲክስ የሀገሪቱን የልማት ትኩረቶች በቀጥታ እንዲመራ የማድረግ ዓላማ ያለው የስታትስቲክስ ፕሮግራም መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
ይህም ቁልፍ የሆኑ ብሔራዊ የቆጠራ ስራዎችን ወቅታዊነትና ሽፋን ማሻሻሉን ጠቅሰው፥ ሀገራዊ የስታትስቲክስ ሥርዓት ውስጥ ተቋማዊ ቅንጅት እንዲጠናከር ማስቻሉን ተናግረዋል።
እንዲሁም ዘመናዊ የመረጃ መሰብሰቢያና መተንተኛ ዘዴዎችን የግብርና እና በሂደት ላይ የሚገኘውን የኢኮኖሚ ተቋማት ቆጠራ በስኬት እያሳለጠ መሆኑንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የስታትስቲክስ ስርዓቷን የማጠናከር ጉዞ በአፍሪካ መረጃን ለማጣጣም፣ የመረጃ ንጽጽር ተመጣጣኝነትን ለማረጋገጥና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ አወጣጥን ለማጎልበት ከሚደረገው ሰፊ ጥረት ጋር ተዛማጅ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ ስታትስቲክስ ማጣጣም ሁለተኛ ስትራቴጂ፣ የአፍሪካ ስታትስቲክስ ቻርተር እና የስታትስቲክስ አፍሪካ ተግባራት ለተቀናጀ የአፍሪካ ስታትስቲክስ ስርዓት አስፈላጊ መሠረት እንደሆኑም አስረድተዋል።
አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላት ተደማጭነትና የአጀንዳዎቿ ተሰሚነት የሚወሰነው በመረጃዎቻችን ጥራት መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም ሚኒስትሩ አፅንኦት ሰጥተዋል።