ቀጥታ፡

የእንስሳት ምርት ጥራትን ለማስጠበቅ ለመኖ አቅርቦትና ለእንስሳት ጤና ክትትል ትኩረት ተሰጥቷል - ግብርና ሚኒስቴር

አዳማ፤ ህዳር 24/2018(ኢዜአ)፦ የእንስሳት ምርት ጥራትን ለማስጠበቅ ለመኖ አቅርቦትና ለእንስሳት ጤና ክትትል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት የእንስሳት ምርት ጥራትን ለማስጠበቅ የጤና ክትትልና መኖ አቅርቦትን ለማሳደግ ስትራቴጂዎች ተቀርጸው ወደ ስራ ገብተዋል።

ስትራቴጂው የኢትዮጵያን እንስሳት ምርት ጥራትን በማረጋገጥ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ላይ ያተከረ መሆኑን አንስተዋል።

የምርት ጥራቱን ለማስጠበቅ የአመጋገብና የእርባታ ሁኔታን አንዲሁም ጤንነታቸው ላይ ጥብቅ ክትትል በማድረግ ከውልደታቸው እስከ ገበያ የሚቀርቡበት ያለውን መረጃ እንደሚያካትትም ተናግረዋል።

በተጨማሪም የእንስሳት ምርታማነትና ጤንነትን የሚጎዱ ድንበር ዘለል በሽታዎችን ለመከላከል የእንስሳት ክትባት፣ የመድኃኒት አጠቃቀምና አያያዝ ህጎችና መመሪያዎች ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የእንስሳት ጤና ክትትል፣ የእንስሳት ጤና ኤክስቴንሽንና የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ባለሙያዎች በየወረዳው ተመድበው በትኩረት እየሰሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የእንስሳት ጤና ላቦራቶሪ ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸው በክልሎች ደረጃ የእንስሳት ጤና ላቦራቶሪዎች የህክምና መርጃ መሳሪያዎች፣ መድሀኒቶችና የላቦራቶሪ ምርመራ ኬሚካሎች እንዳሉ አስረድተዋል።


 

የኢትዮጵያ እንስሳት ህክሞች ማህበር ፕሬዘዳንት ዶክተር ቦጃ ሂንደቡ፤ ማህበሩ ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት የእንስሳት ሀብት ምርታማነት እንዲጨምር የሚደረገውን ጥረት እያገዘ ይገኛል ብለዋል።

አዳዲስ አሰራሮች፣ ስትራቴጂዎችና አዋጆች መውጣታቸው የእንስሳት ሀኪሞች በላቦራቶሪ አገልግሎት፣ በክትባት፣ በልየታና የኋልዮሽ ታሪክ ክትትል ላይ በሙያቸው እንዲሳተፉ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም