የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር አብሮነትን ከማጠናከር ባለፈ ልማትን ለማፋጠን ቃላችንን የምናድስበት ነው - ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር አብሮነትን ከማጠናከር ባለፈ ልማትን ለማፋጠን ቃላችንን የምናድስበት ነው - ተሳታፊዎች
ዲላ፤ ህዳር 24/2018(ኢዜአ)፦ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር አብሮነትን ከማጠናከር ባለፈ ልማትን ለማፋጠን ዳግም ቃላችንን የምናድስበት ነው ሲሉ በቡሌ ሆራ ከተማ በተከበረው መርሃ ግብር የተሳተፉ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተሳታፊዎች ገለጹ።
20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ከተለያዩ አካባቢ የመጡ የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች በተገኙበት በቡሌ ሆራ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
በዓሉን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው ተሳታፊዎች እንደገለጹት በዓሉ የእርስ በርስ ትውውቃቸውን ከማሳደግ ባለፈ ልማትን ለማፋጠን ዳግም ቃላቸውን የሚያድሱበት መሆኑን ተናግረዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የቡርጂ የባህል አባት መሐመድ ወሌ ቀኑ እርስ በርስ በመተዋወቅ ግንኙነትን በማጠናከር ሀገራዊ አንድነታችንን የምናጸናበት ነው ብለዋል።
በበዓሉ ላይ ባህላዊ እሴቶቻችንን ከማስተዋወቅ ባለፈ በየአካባቢያችን የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን ዳግም ቃላችንን የምናድስበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች በተገኙበት በዓሉ በጋራ መከበሩ የተለየ ስሜት እንደፈጠረበቸው ያነሱት ሌላው የበዓሉ ተሳታፊ ደግሞ የቦረና ዞን ሃደ ሲንቄ ጡሩ ሞሉ ናቸው።
ቀኑ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህሎች እንዲሁም የአኗኗር ዘይቤያቸውን ለማወቅና የራሳቸውንም ለማስተዋወቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው ጠቅሰዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በጋራ ቆመን እንዳሳካነው ሁሉ ሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን አጠናቀን ሀገራዊ ብልጽግናን ለማሳካት አንድነትን ማጠናከር አለብን ብለዋል።
ከጉራጌ ዞን የመጣችው ወጣት በጽናት ተመስገን በበኩሏ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ሕብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ለዓለም ለማሳየት ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ብላለች።
በተለይ ኢትዮጵያ የተለያዩ ቀለሞች፣ ባህሎችና ቋንቋዎች ባለቤት መሆኗን ገልጸው፤ በዓሉ አብሮነታችንና አንድነታችንን በማጠናከር ለልማትና ለሰላም በጋራ ለመቆም ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም አንስታለች።
በኦሮሚያ ክልል ደረጃ 20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር እና የተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች በተገኙበት በቡሌ ሆራ ከተማ መከበሩ የሚታወስ ነው።