ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጠንካራ፣ ዘመናዊና የተቀናጀ ስታትስቲካዊ ሥርዓትን በትብብር ለመገንባት ቁርጠኛ ናት - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 24/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአፍሪካን የልማት አጀንዳ የሚደግፍ ጠንካራ፣ ዘመናዊና የተቀናጀ ስታትስቲካዊ ሥርዓትን በትብብር ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።

19ኛው የአፍሪካ ብሔራዊ ስታትስቲክስ ዋና ዳይሬክተሮች ኮሚቴ ስብሰባ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፥ በአፍሪካ ላሉ ውስብስብ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የስነ-ህዝብና የአካባቢ ችግሮች ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት ወቅታዊ፣ እምነት የሚጣልበትና የተጣጣመ የስታትስቲክስ መረጃ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ስታትስቲክስ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ዕቅድና በመረጃ የሚመራ ልማትን ለማከናወን የጀርባ አጥንት ነው ብለዋል።

ዘመናዊ የአፍሪካ ስታትስቲካዊ ሥርዓት ተጨባጭ ውጤት የሚያመጡ ፖሊሲዎችን ለመቅረጽ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ብሔራዊ የልማት ዕቅዶችን ለመንደፍ፣ የመንግሥትን በጀት በአግባቡ ለመምራት፣ ሥራ አጥነትን ለመቀነስና ከአየር ንብረት መዛባት እስከ ገበያ መዋዠቅ ድረስ ያሉ ቀውሶችን ለመቋቋም በአስተማማኝ መረጃ ላይ የተመሠረተ አሠራርን መከተል የግድ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ጠንካራ የስታትስቲክስ ስርዓትን ለመገንባት እየሠራች ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአስር ዓመት የልማት ዕቅዷና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በጠንካራ መረጃ ላይ ተመስርተው መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።

ምርታማነትን ማሻሻል፣ የምግብ ሥርዓትን ማሳደግ፣ መሠረተ ልማትን ማስፋፋትና የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማረጋገጥ ትክክለኛ ስታትስቲክስ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ሥራዎቹን እያዘመነ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዲጂታል መረጃ አሰባሰብን በማስፋት፣ የአስተዳደር መረጃ ሥርዓቶችን በማሻሻልና ወሳኝ የሆኑ የቤተሰብ፣ የኢኮኖሚና የሌሎች ዘርፍ ስታትስቲክስን በማመንጨት ላይ ይገኛል ብለዋል።

እነዚህ ጥረቶች ብሔራዊ የልማት ትግበራችንን የምንመራበትን የመረጃ አስተማማኝነት ያሳድጋሉ ነው ያሉት።


 

በቀጣይ በአፍሪካ ጠንካራ የስታትስቲክስ ሥርዓት ለመገንባት የስታትስቲክስ አስተዳደርንና ተቋማዊ ነጻነትን ማጠናከር፣ በቂና ቀጣይነት ያለው የስታትስቲክስ ፋይናንስን ማረጋገጥ እንዲሁም በአፍሪካ የስታትስቲክስ ውህደትና ተናባቢነትን ማጎልበት እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል።

ልማት በምኞት ሳይሆን በእውቀት፣ በትክክለኛ የስታትስቲክስ የትንተና አቅምና በመረጃ ላይ በተመሠረተ ትግበራ እንደሚሳካ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

አስተማማኝ ስታትስቲክስ ልማትን የምንመራበት ካርታ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁናዊ አፈጻጸምን በማሳየት መዳረሻችንንና መንገዱን ያመላክታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካን የልማት አጀንዳ የሚደግፍ ጠንካራ፣ ዘመናዊና የተቀናጀ ስታትስቲካዊ ሥርዓትን ለመገንባት ከሁሉም አባል ሀገራትና ከልማት አጋሮች ጋር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም