ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት እይታ የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጥ ጥልቅ እሳቤ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ እንተጋለን - የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች

አዳማ፤ ህዳር 24/2018 (ኢዜአ)፦ የመደመር መንግስት እይታ የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጥ ጥልቅ እሳቤ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ እንተጋለን ሲሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ!” በሚል መሪ ሃሳብ ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ሰፊ እና ጥልቅ የሆነ ስልጠና መስጠታቸው ይታወቃል።

በስልጠናው በተለይም በመንግስት አስፈፃሚ አካላት የሚተኮርባቸውን ግቦች በዝርዝር ያስረዱ ሲሆን በመፍጠርና በመፍጠን የሚተገብር ቁርጠኛ አመራር መኖር እንዳለበትም አጽኖት ሰጥተዋል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ የኢዜአ ሪፖርተር በአዳማ ከተማ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ያነጋገረ ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ አቅጣጫዎች ሀገርን መለወጥ የሚችሉና ህዝብን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስለመሆናቸው አንስተዋል። 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የአዳማ ከተማ ነዋሪና የአዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ጋረደው ጅማ፤ በተለይም ተረጅነትን፣ መንደርተኝነትን፣ መሬት ፆም ማሳደርንና ሽፍትነትን ዜሮ ማድረግ የጋራ አጀንዳችን ይሆናል ብለዋል።

የበጋ መስኖ፣ የሌማት ትሩፋት፣ ኩታ ገጠም እርሻና ሌሎችም ኢንሸቲቮች የለውጥና ተጠቃሚነት መሰረቶች መሆናቸውንም አንስተዋል።

በመሆኑም የመደመር መንግስት እይታ የኢትዮጵያን ቀጣይ እጣ ፋንታ የሚወስኑ ጥልቅ እሳቤዎች በመሆናቸው ለተግባራዊነቱ በጋራ መትጋት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በትምህርት ዘርፍ ከተያዘው አቅጣጫ አንፃር የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና አንዱ መሆኑን አንስተው በርካታ ወጣቶችና በየዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች የእድሉ ተጠቃሚ ስለመሆናቸው አስታውሰው በተጣነከረ መልኩ መቀጠል ያለበት ጉዳይ ነው ብለዋል።

በሌሎችም መስክ ለተያዙ የልማት ውጥኖች መሰካት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ህብረተሰቡን በማሳተፍ በጊዜ የለንም መንፈስ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ገልፀዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ተካልኝ ደንደአ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለከፍተኛ አመራሮች የተሰጠው ስልጠና የኢትዮጵያ እድገትና ማንሰራራት የሚወስኑ ጥልቅ ሃሳቦች መሆናቸውን ተናግረዋል። 

በኢትዮጵያ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ በተለይም የአመራሩ የመፈፀም አቅምና ቁርጠኝነት የግድ ቢሆንም ያለ ህዝብ ተሳትፎና እገዛ የማይሳካ በመሆኑ የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን በማለትም አረጋግጠዋል።

በመንግሥት የተያዘው አቅጣጫ በተወሰኑ አካላት ጥረት ብቻ  የሚሳካ ባለመሆኑ በትብብርና በመደመር እሳቤ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የደጋጋ ወረዳ ነዋሪ የሆነው ወጣት መልካሙ አብዲሳ፤  የመልማት ፍላጎቶቻችን በመንግስት አቅም ብቻ የሚከወኑ ባለመሆኑ ለስኬቱ በጋራ እንሰራለን ብሏል።

በተለይ  የሀገር  ልማት የትውልድ አሻራ ሥራ በመሆኑ አመራሮች የተሰጣቸውን አቅጣጫ ለማስፈጸም ከመደርተኝነት፣ ከሌብነት እና ብልሹ አሰራር በፀዳ መልኩ ለሀገር እድገትና ብልጽግና የድርሻችንን እንወጣለን በማለት ተናግሯል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም