በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን የመኸር ሰብል በሜካናይዜሽን ታግዞ እየተሰበሰበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን የመኸር ሰብል በሜካናይዜሽን ታግዞ እየተሰበሰበ ነው
ጅግጅጋ፤ ህዳር 24/2018(ኢዜአ):- በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን አወበሬ ወረዳ የመኸር ሰብል በሜካናይዜሽን ታግዞ እየተሰበሰበ መሆኑን የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የሶማሌ ክልል ሰፊ ለም መሬት እና በርካታ የውሃ አማራጮች ያሉት ቢሆንም ከእንስሳት እርባታ ባለፈ ለግብርና ሥራ ሳይውል ቆይቷል።
ከለውጡ ወዲህ አርብቶ አደሩ ከእንስሳት እርባታው በተጓዳኝ በግብርናው ዘርፍ በመሰማራት የምግብ ሉዓላዊነቱን እንዲያረጋግጥ በተሰሩ ስራዎች አስደናቂ ለውጦች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
ለዚህም የክልሉ መንግሥት የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ሕዝቡ ልማት ላይ እንዲያተኩር በማድረጉ ሰፊ መሬት ለማልማት ተችሏል።
በክልሉ የስንዴ እርሻ ልማት በሰፊው ከሚከናወንባቸው ዞኖች መካከል ደግሞ የፋፈን ዞን አንዱ ነው።
በዞኑ አወበሬ ወረዳ በመኸር አዝመራው የለማ ስንዴ ከብክነት በጸዳ መልኩ በሜካናይዜሽንና በሰው ኃይል ታግዞ እየተሰበሰበ ይገኛል።
የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ ኢደሌ ሙሴ ለኢዜአ እንደገለጹት በወረዳው በመኸር ወቅት ዋና ዋና የምግብ ሰብሎች እንደ ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ ማሽላ እና ሌሎችም መልማታቸውን ገለጸዋል።
በ2017/18 የመኸር ወቅት በወረዳው በዘር ከተሸፈነው 115 ሺህ 121 ሄክታር ውስጥ 82ሺህ 150 ሄክታሩ በስንዴ መልማቱን ገልጸዋል።
በመኽር ሰብል ከተሸፈነው መሬትም ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸው፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለአርሶ አደሩ የምርጥ ዘርና ሌሎች ግብዓቶች በጊዜው መሰራጨቱን ተናግረዋል።
በወረዳው የደረሱ ሰብሎችን በኮምባይነር በመሰብሰብ የአርሶ አደሩ ጉልበትና ጊዜን ለመቆጠበ እንዲሁም የሰብል ብክነት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የመኸር እርሻው ሰብል ከተሰበሰበ በኋላ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በትኩረት እንደሚሰራም አክለዋል።