ዘጠኝ ግቦች በተቆጠሩበት አዝናኝ ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ ፉልሃምን አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
ዘጠኝ ግቦች በተቆጠሩበት አዝናኝ ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ ፉልሃምን አሸነፈ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 23/2018(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ14ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ማንችስተር ሲቲ ፉልሃምን 5 ለ 4 አሸንፏል።
ማምሻውን በክራቫን ኮቴጅ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፊል ፎደን ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አርሊንግ ሃላንድ፣ ታጃኒ ራይንደርስ እና የፉልሃሙ ሳንደር በርገ በራሱ ላይ ቀሪዎቹን ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ሳሙኤል ቹኩዌዜ ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ኤሚል ስሚዝ ሮው እና አሌክስ ኢዎቢ ቀሪዎቹን ግቦች ለፉልሃም አስቆጥረዋል።
ማንችስተር ሲቲ 5 ለ 1 እየመራ ሶስት ግቦችን ማስተናገዱ በጨዋታው ማብቂያ ላይ ውጥረት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።
በሊጉ ዘጠነኛ ድሉን ያስመዘገበው ማንችስተር ሲቲ በ28 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ ሰባተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ፉልሃም በ17 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል።
አርሊንግ ሃላንድ በሊጉ 100ኛ ግቡን አስቆጥሯል። ሃላንድ በሊጉ ፈጣን 100 ግብ አስቆጣሪ በመሆን አዲስ ታሪክ ሰርቷል። ተጫዋቹ ግቦቹን ከመረብ ላይ በማሳረፍ 111 ጨዋታዎች ወስዶበታል።
ከዚህ ቀደም አለን ሺረር በ124 ጨዋታዎች 100 ግቦችን በማስቆጠር ለ30 ዓመታት ክብረ ወሰኑን ይዞ ቆይቷል።
በሌሎች መርሃ ግብሮች ኤቨርተን በጃክ ግሪሊሽ ጎል ቦርንማውዝን ከሜዳው ውጪ 1 ለ 0 አሸንፏል።
ኒውካስትል ዩናይትድ እና ቶተንሃም ሆትስፐርስ ያደረጉት ጨዋታ ሁለት አቻ ተጠናቋል።
ብሩኖ ጉማራይሽ በጨዋታ እና አንቶኒ ጎርደን በፍጹም ቅጣት ምት ለኒውካስትል ግቦቹን አስቆጥረዋል ።
ክርስቲያን ሮሜሮ ለቶተንሃም ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፏል።