ቀጥታ፡

ጎንደር ዩንቨርሲቲ ሙስናን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በምርምርና አሰራር በመደገፍ የድርሻውን እየተወጣ ነው

ጎንደር፤ ሕዳር 23/2018(ኢዜአ)፡- ጎንደር ዩንቨርሲቲ የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከል የሚደረገውን  ጥረት  በምርምርና አሰራር በመደገፍ  የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን  ገለጸ። 

ዩንቨርሲቲው "ትውልድን በስነ ምግባር ተቋምን በአሰራር’’ በሚል መሪ ሀሳብ 22ኛውን የዓለም የፀረ ሙስና ቀን  በፓናል ውይይት  አክብሯል፡፡


 

በዚህ ወቅት  የዩንቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን(ዶ/ር)፤ የሀገርን የኢኮኖሚና የዜጎችም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ እንቅፋት የሆነውን ሙስና   መከላከል ላይ  በቅንጅት መስራት ይገባል  ብለዋል፡፡

ሙስና  የዘመናት ችግር ሆኖ የዘለቀ መሆኑን አንስተው፤  ከለውጡ ወዲህ መንግስት ለፀረ ሙስና ትግሉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ  የአሰራርና የህግ ማእቀፎችን በማዘጋጀት የሙስና ወንጀል ፈጻሚዎች ለሕግ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንግስት ሙስናን  የመከላከል  ተግባርና ጥረት  ውጤታማ እንዲሆን  በምርምር  በመደገፍ   ረገድ  ዩኒቨርሲቲው  የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡  


 

ዩኒቨርሲቲው የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ከማቋቋም ጀምሮ በሰለጠነ የሰው ሃይልና በግብአት በማጠናከር ለሙስና የተጋለጡ አሰራሮችን ከሰው ንክኪ ነፃ የሆኑ አሰራር ማመቻቸቱንም አንስተዋል፡፡ 

ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ  የስራ ክፍሎችን በመለየት አሰራሮችን የመፈተሸና የመከታተል ስራዎች እየተካሄደ ነው ያሉት የዩኒቨርሲቲው የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ተወካይ ወይዘሮ ንግስት መኮንን ናቸው፡፡


 

ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ከመዘርጋት ጀምሮ ተቋሙን በአሰራርና በአደረጃጀት በማዘመን ቀልጣፋና ፍትሃዊ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሙስናን መታገል የምርጫ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ  መሆኑን ገልጸው፤ ተማሪዎችን በስነ ምግባር ከማነጽ ጀምሮ በፀረ ሙስና ትግሉ የስነ ምግባር አምባሳደር በመሆን የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ሰራተኞች በኦን ላይን የሀብት ማሳውቅና የማስመዝገብ ስራ እንዲያካሂዱ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ወደ ስራ መገባቱንም አንስተዋል፡፡

በፓናል ውይይት ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ፣መምህራን ፣ተማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም