ቀጥታ፡

የኃይማኖት ተቋማት ፍቅርን፣ ሰላምንና አብሮነትን ማስተማር ይጠበቅባቸዋል - ጉባኤው

ነቀምት፤ ህዳር 23/2018(ኢዜአ)፦ የኃይማኖት ተቋማት ከሁሉም ነገር በፊት ፍቅርን፣ ሰላምንና አብሮነትን ማስተማር እንደሚጠበቅባቸው የነቀምቴ ከተማ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ።

የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከሃይማኖት ተቋማት አባቶች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት የነቀምቴ ከተማ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ቄስ አስፋው ተረፍሳ፤ የኃይማኖት ተቋማት ዋነኛ ተግባር ፍቅርን፣ ሰላምንና መተሳሰብን በማስተማር ሰላምን ማጽናት መሆኑን አንስተው በዚህ ረገድ ተቋማቱ የመንግስትን ጥረት በማገዝ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ጉባኤው ከተቋቋመ ጀመሮ በዚህ ዙሪያ በስፋት እየሰራ መሆኑን አንስተው ይህንኑ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምስራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅና የጉባኤው አባል ቄስ ገረመው በቀለ፤ በየቤተ እምነቱ የሚሰጡ አስተምህሮዎች ለሀገር ሰላምና ለትውልድ ግንባታ ትልቅ አቅም መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ቀጣይነት ያለው ተግባር ከተቋማቱ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

የነቀምቴ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ኃላፊ ሼህ ተማም ሞሀመድ፤ በበኩላቸው የእምነት ተቋሞቻችን ለሀገር ሰላምና ለትውልድ ግንባታ ትልቅ አበርክቶ አላቸው ብለዋል።

በመሆኑም በየድርሻችን ሰላምን፣ ፍቅርንና አብሮነትን በማስተማር ከምንም በላይ ለሀገርና ለትውልድ ግንባታ አደራችንን ልንወጣ ይገባል ነው ያሉት።

የኃይማኖት አባቶች እያደረጉት ባለው ያለሰለሰ ጥረትም በተለያዩ አካባቢዎች የሰፈነውን ሰላም በማዝለቅ የልማት ተግባራት እንዲጠናከሩ ትልቁን ድርሻ እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሀይማኖት አባቶች ሰላምና አብሮነት ዙሪያ የሚያስተላልፉት አስተምህሮ ለሀገር ልማትና ዘላቂ ሰላም የራሱን ድርሻ እየተወጣ ነው ያሉት ደግሞ የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ መሰረት ሀይሉ ናቸው።

በዚህም በከተማዋ የሰፈነውን ሰላም በማዝለቅ የተጀመረው የብልፅግና ጉዞ እንዲሳካ የኃይማኖት አባቶቹ እያከናወኑት ያለውን ተግባር አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም