ለሀገራዊ ምክክሩ ቀጣይ ስራዎች የሀይማኖት ተቋማትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አስተዋጽኦ የበለጠ መጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ምክክሩ ቀጣይ ስራዎች የሀይማኖት ተቋማትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አስተዋጽኦ የበለጠ መጠናከር አለበት
አዲስ አበባ፤ ህዳር 23/2018(ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ ምክክር ቀጣይ ስራዎች የሀይማኖት ተቋማትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ የበለጠ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ አስታወቁ።
ኮሚሽኑ ወደ ምክክር ሂደቱ ለመሸጋገር የሚያስችሉ ወሳኝ የሆኑ ቀሪ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ "የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማትና የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች የላቀ ተሳትፎ ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ አካሄዷል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኮሚሽኑ ምክክሩ ሁሉን አሳታፊና አካታች እንዲሆን ለተሳታፊ ልየታ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
በዚህም የኅብረተሰብ ክፍሎችን፣ የሃይማኖት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን፣ በርካታ ተቋማትና ማህበራትን፣ ታዋቂ ሰዎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዲሁም መንግሥትን በተወካዮቻቸው አማካኝነት ማካተትና ማሳተፍ መቻሉን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይወሰን ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሂደቱ እንዲሳተፉ ጥረት ማድረጉን አንስተዋል።
ኮሚሽኑ ጉባዔው የሚመክርባቸውን አጀንዳዎች ይፋ ለማድረግና ጉባዔውን ለመጥራት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን አስታውቀው፤ ለዚህም ዝግጅቶችን እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ከፍተኛ አመራር አባለት፣ የሀይማኖት ተቋማት ጉባዔና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የካበተ ልምድ ስላላቸው ቀሪ ስራዎች እንዲሳኩ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክነት የህግ አገልግሎት መምሪያ ኃላፊ መምህር አባ ገብረሥላሴ ጌትነት እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ምክክር ለሀገር መንግስት ግንባታ ወሳኝ ጉዳይ ነው።
ለምክክሩ ስኬታማነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ዑስታዝ ተምኪን አብዱላሂ፤ ኮሚሽኑ ስኬታማ ስራ ማከናወኑን ተናግረው፤ ከዚህ በፊት ተሳትፎ ያላደረጉ አካላት እንዲሳተፉ የበኩላችንን ሃላፊነት እንወጣለን ብለዋል።
በኢትዮጵያ ወንጌላውያን ቤተክርስቲያናት ህብረት የአዲሰ አበባ የቦርድ ሰብሳቢ መጋቢ ሲሳይ መላኩ (ዶ/ር) ኮሚሽኑ እያከናወነ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን አንስተው፤ ቀሪ ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ትብብራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ተረፈ ደጌቲ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልፀው፤ በቀጣይ የሚከናወኑ ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።