ቀጥታ፡

ምሁራን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ሀሳቦችን በማፍለቅ ዘላቂ ሰላምን የማፅናት ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል

ደብረማርቆስ፤ ሕዳር 23/2018(ኢዜአ)፡- ምሁራን ሀገር አሻጋሪ እና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ሃሳቦችን በማፍለቅ ዘላቂ ሰላምን የማፅናት ሚናቸውን ይበልጥ መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ/ር) በወቅታዊና ሰላም ግንባታ ጉዳይ ዙሪያ ዛሬ ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ተወያይተዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ ዩኒቨርሲቲዎች ከመማር ማስተማር ስራቸው በተጓዳኝ ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሄዎችን የማቅረብ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

በመሆኑም በተለይ ምሁራን ሀገር አሻጋሪ እና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን አጠናካሪ ሃሳቦችን በማፍለቅ ዘላቂ ሰላምን ለማፅናት ሚናቸውን ይበልጥ መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

ቸግሮች በሰላማዊ ውይይት እንዲፈቱ መንግስት በሆደ ሰፊነት ረጅም ርቀት በመሄድ ሲሰራ መቆየቱን አውስተው፤ይህንን ተግባር አሁንም አጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።




የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳይህ ካሳው(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ተቋሙ ሰላምን በመደገፍ የመማር ማስተማሩን ስራ ለማሳካት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

የሰላም ጉዳይ የጋራ ስለሆነ በሕብረት መስራታችንን አጠናክረን መቀጠል ይገባናል ብለዋል።

ሰላምን በዘላቂነት አፅንቶ ለማስቀጠል ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት አለብን ያሉት ደግሞ የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ናቸው።

ምሁራን እውቀታቸውን ለሰላም እና ለልማት ግንባታ በማዋል ድጋፋቸውን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊ ምሁራን መካከል የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ይኼይስ አረጉ(ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፤ መንግስት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እያደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ የድርሻችንን መወጣት ይገባናል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር በእውቀት ሲሳይ በበኩላቸው፤ ሰላምን ማፅናት የእያንዳንዳችንን ተሳትፎ የሚጠይቅ ስለሆነ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም