ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከሠራተኛ ማኅበራት መብቶች ጋር በተያያዘ ያስመዘገበቻቸው ጉልህ መሻሻሎች የሚደነቁ ናቸው - ዓለም አቀፉ የሠራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን

አዲስ አበባ፤ ህዳር 23/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከሠራተኛ ማኅበራት መብቶች ጋር በተያያዘ ያስመዘገበቻቸው ጉልህ መሻሻሎች የሚደነቁ መሆናቸውን የዓለም አቀፉ የሠራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ዋና ጸሐፊ ሉክ ትራያንግል ገለጹ።

የዓለም አቀፉ የሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።


 

የዓለም አቀፉ የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ዋና ጸሐፊ ሉክ ትራያንግል በዚሁ ወቅት እንዳሉት ስብሰባው በኢትዮጵያ መካሄዱ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ጉልህ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ያለች ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ ይህም የድህነት መጠን እንዲቀንስ እና እንደ ጤናና ትምህርት ባሉ ማህበራዊ ዘርፎች ላይ መሻሻሎችን ማምጣቱን ተናግረዋል።


 

ሀገሪቱ በአስደናቂ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ጉዞ ላይ ናት ያሉት ዋና ጸሐፊው ከሠራተኛ ማኅበራት መብቶች ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ውስጥ ጉልህ መሻሻል መኖሩን ጠቁመዋል።

በዓለም ዙሪያ ሠራተኞች እየተጋፈጧቸው ያሉ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮችን ለመፍታት ጠንካራና ድንበር ተሻጋሪ ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው በኢትዮጵያ መንግስት እና ሕዝብ አረንጓዴ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር፣ የኢንዱስትሪ አቅምን ለማስፋት፣ ታዳሽ ኃይልን ለማስፋፋት እና ብሔራዊ ኢኮኖሚን ለማጠናከር በጋራ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የሠራተኛውን ማህበረሰብና የአጠቃላይ ህዝቡን የኑሮ ሁኔታ የሚቀይሩ እንዲሁም ለሚቀጥለው ትውልድ ምቹ የሥራና የኑሮ ምህዳርን ለመፍጠር መሰረት የሚጥሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

የሠራተኛ ገበያው እየተለወጠ እና አዳዲስ የሥራ ዓይነቶች እየተፈጠሩ ሲመጡ የሠራተኛ ማኅበራት የሚገጥሟቸው ፈተናዎች ለመሻገር የጋራ እና የተቀናጀ መፍትሄዎችን እንደሚሹም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም