ታንዛንያ ከ17 ዓመት የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ዋንጫን አነሳች - ኢዜአ አማርኛ
ታንዛንያ ከ17 ዓመት የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ዋንጫን አነሳች
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 23/2018 (ኢዜአ)፦ በ16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣሪያ ፍጻሜ ጨዋታ ታንዛንያ ዩጋንዳን 3 ለ 2 አሸንፋለች።
በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ራዛኪ ምቤጌሌንዲ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ሉክማን ምባላሳሉ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ቶማስ ኦጌማ እና ብሪያን ኦልዋ ለዩጋንዳ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ታንዛንያ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ አሸናፊ ሆናለች። ዩጋንዳ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ሀገራቱ በምድብ ሁለት ተገናኝተው ታንዛንያ 2 ለ 0 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።
ታንዛንያ እና ብሩንዲ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸው ይታወቃል።
ዛሬ በተደረገ የደረጃ ጨዋታ አዘጋጇ ኢትዮጵያ ኬንያን 3 ለ 0 በማሸነፍ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፏን አረጋግጣለች።
ከሕዳር 6 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የነበረው የሴካፋ ማጣሪያ ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል።
በውድድሩ ከአንድ እስከ ሶስተኛ የወጡት ታንዛንያ፣ ዩጋንዳ እና ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2026 ሞሮኮ በምታስተናግደው 16ኛው ከ17 ዓመት የአፍሪካ ዋንጫ ሴካፋ ዞንን ወክለው ይሳተፋሉ።
በአፍሪካ ዋንጫው 16 ሀገራት ተሳታፊ ናቸው።