በምስራቅ ጎጃም ዞን ሰላምን በማጽናትና ልማትን በማረጋገጥ በህዝቡ የታየው ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ጎጃም ዞን ሰላምን በማጽናትና ልማትን በማረጋገጥ በህዝቡ የታየው ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
ደብረ ማርቆስ፤ ህዳር 23/2018 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ጎጃም ዞን ሰላምን በማጽናትና ልማትን በማረጋገጥ ረገድ በህዝቡ ዘንድ የታየው እገዛና ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ በሰላምና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በደብረ ማርቆስ ከተማ ከነዋሪዎችና ከተለያዩ የህብረተሰቡ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በክልሉ የጥፋት ተልእኮ በመያዝ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር፣ የልማት ስራዎች እንዳይሳኩና ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲስተጓጎሉ ፅንፈኞች ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የጽንፈኛ ቡድኑ የጥፋት ተልእኮ ግን በህዝቡ ጠንካራ ትብብርና በጸጥታ ኃይሉ ህግ የማስከበር እንቅስቃሴ በሁሉም አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ተችሏል ብለዋል።
ለዚህም የህዝቡ ትብብር፣ እገዛና ጽኑ የሰላም ፍላጎት ታክሎበት ችግሩን መፍታት ስለመቻሉ አንስተው ሰላምን በማጽናትና ልማትን በማረጋገጥ ረገድ የህዝቡ እገዛና ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በሁሉም አካባቢዎች ያለውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል መንግስት እየሰራ መሆኑን ገልጸው የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ በማቋቋም ሰላማዊ ህይወት እንዲመሩ እየተደረገ ነው ብለዋል።
አሁንም ቢሆን በጫካ የሚገኙ የታጠቁ ቡድኖች የሰላም እድሉን ከተጠቀሙ ምንጊዜም በሩ ክፍት ስለመሆኑ አረጋግጠዋል።
ከዚህ ባለፈ ግን ሰላምን የማስጠበቅና ልማትን የማረጋገጥ ስራ በተቀናጀና በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ፤ ከነዋሪዎች ጋር በመተባበር በተሰራው ስራ የከተማዋ ሰላም በመልካም ሁኔታ ላይ እንዲገኝ አስችሏል ብለዋል።
የዚህ መድረክ ዓላማም የተገኘውን ሰላም ማጽናትና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል መሆኑን ገልጸዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ እስራኤል እምባቆም እና ወይዘሮ መስከረም ታደገ፤ የሰላም ጉዳይ በጋራ አቋም ይዘን የምንሰራበት በመሆኑ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ተሳትፈዋል።