ቀጥታ፡

የይርጋ ዓለም ሆስፒታል ህክምና ኮሌጅ አገልግሎት መሻሻል እንግልትንና አላስፈላጊ ወጪን አስቀርቶልናል-ተገልጋዮች

ሀዋሳ፤ ህዳር 23/2018 (ኢዜአ)፡- የይርጋ ዓለም ሆስፒታል ህክምና ኮሌጅ አገልግሎት መሻሻል እንግልትንና አላስፈላጊ ወጪን እንዳስቀረላቸው ተገልጋዮች  ገለጹ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የይርጋዓለም ሆስፒታል ህክምና ኮሌጅ ተገልጋዮች እንደተናገሩት የሆስፒታሉ አገልግሎት እየተሻሻለ መጥቷል፡፡

የአገልግሎቱ መሻሻልም ከዚህ ቀደም ይገጥማቸው የነበረን እንግልትንና አላስፈላጊ ወጪን እንዳስቀረላቸው ገልጸዋል።

ከሆስፒታሉ ተገልጋዮች መካከል የይርጋዓለም ከተማ ነዋሪው አቶ ምስጉን ታደገ በሆስፒታሉ የጥርስ ህክምና አገልግሎት ቅልጥፍናና  እንክብካቤ  መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በሆስፒታሉ የአገልግሎት ጥራት መሻሻልን ከአቶ ምስጉን ጋር የሚጋሩት የዳሌ ወረዳ ነዋሪው ወጣት አሥራት ቱርጋሞ የአጥንት ውልቃት አደጋ ገጥሞት በሆስፒታሉ ህክምና ማግኘቱን ተናግሯል፡፡

በሆስፒታሉ ተኝቶ ህክምና ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው ያገኘናቸው የይርጋዓለም ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ መሠረት ዘውዴ በበኩላቸው ከህመማቸው በቀናት ውስጥ አገግመው ጤናቸው መሻሻሉን አስረድተዋል፡፡

በሆስፒታሉ የሚሰጠው አገልግሎት የተሻሻለ መሆኑንና በሁሉም ደረጃ ያሉ የህክምና ባለሙያዎች ትጋትና ትህትና የሚደነቅ መሆኑን  ገልጸዋል ፡፡

የሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዘሪሁን ነጋሽ የሆስፒታሉን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሰው ኃይል ልማትና ቁሳቁስ ማሟላት ላይ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

ሆስፒታሉ የአገልግሎት ጥራቱን ለማስጠበቅ ከ40 በላይ ስፔሻሊስትና ሰብ ስፔሻሊስት ሀኪሞችን በመያዝ አዳዲስ የህክምና አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡

ለአብነትም የካንሰር ተመላላሽ ህክምና፣ የጉበት ቀዶ ጥገና እንዲሁም የመንጋጋና ጥርስ ህክምናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

በቅርቡም የካንሰር ተኝቶ ህክምና፣ የአንገት በላይ ቀዶ ህክምናና የነርቭ ቀዶ ህክምና አገልግሎቶችን ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ሆስፒታሉ ከ200 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተመላላሽና ተኝቶ ታካሚዎች አገልግሎት መስጠቱን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም