ኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ አለፈች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ አለፈች
አዲስ አበባ፤ሕዳር 23/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣሪያ ከኬንያ አቻው ጋር ባደረገው የደረጃ ጨዋታ 3 ለ 0 በማሸነፍ ለአህጉራዊው መድረክ ማለፉን አረጋግጧል።
በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ዳዊት ካሳው በ66ኛው ፤ አምበሉ ቢነያም አብርሃ በ79ኛው እና ብሩክ እይላቸው በ93ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥረዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2026 በሞሮኮ አስተናጋጅነት በሚካሄደው 16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማለፏን ያረጋገጠች ሶስተኛ ሀገር ሆናለች።
በውድድሩም ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሳተፈችው እ.አ.አ በ2003 ስዊዚላንድ ባዘጋጀችው ውድድር ላይ ነበር።
ከ22 ዓመታት በኋላ በውድድሩ ላይ ትሳተፋለች።
ኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ላይ ስትሳተፍ የሞሮኮው ለአራተኛ ጊዜ ነው።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን አጥቂ ዳዊት ካሳው በውድድሩ ላይ ያስቆጠራቸውን ግቦች ብዛት ወደ ስምንት ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን አጠናቋል።
ታንዛንያ እና ዩጋንዳ ሌሎች ለአፍሪካ ዋንጫው ያለፉ ሀገራት ናቸው።
የሴካፋ ማጣሪያ የፍጻሜ ጨዋታ በታንዛንያ እና ኬንያ መካከል ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ላይ በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ይካሄዳል።
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከሕዳር 6 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣሪያ ዛሬ ይጠናቀቃል።
በውድድሩ ላይ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የሚወጡ ሀገራት የሴካፋ ዞንን ወክለው እ.አ.አ በ2026 በሞሮኮ አስተናጋጅነት በሚካሄደው 16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መረጃ ያመለክታል።