የበደልነውን ሕዝብ ለመካስ ተዘጋጅተናል- የቀድሞ ታጣቂዎች - ኢዜአ አማርኛ
የበደልነውን ሕዝብ ለመካስ ተዘጋጅተናል- የቀድሞ ታጣቂዎች
ገንዳ ውሃ ፤ ሕዳር 23/2018 (ኢዜአ)፦ የተሳሳተ መንገድ ተከትለው በፈፀሙት ጥፋት በመፀፀት የበደሉትን ሕዝብ ለመካስ መዘጋጀታቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን የሰላም አማራጭ ተቀብለው የተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች ተናገሩ።
በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ በዳንስ ጉንዶ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ ተቀብለው በመመለስ ሙሉ ትጥቃቸውን ለመንግስት አስረክበዋል።
ከእነዚህም መካከል መብራቱ አወቀ በሰጠው አስተያየት፤ በተሳሳተ መንገድ ለጥፋት በመንቀሳቀስ ሕዝቡንና አካባቢውን ለችግር በማጋላጣቸው መፀፀቱን ተናግሯል።
ችግርን በሰላማዊ ውይይት መፍታት ሲገባ ግጭት በመቀስቀስ ጥፋት መፈፀም ተገቢነት እንደሌለው በመገንዘብ የሰላም አማራጭ መቀበላቸውን አመልክቶ፤ የተሳሳተ መንገድ ተከትለን በፈፀምነው ጥፋት ተፀፅተን የበደልነውን ሕዝብ ለመካስ ተዘጋጅተናል ብሏል።
የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል አብረውት ከነበሩት ጋር መመለሳቸውን የገለጸው ደግሞ ሌላው የቀድሞ ታጣቂ አየነው ውበት ነው።
የተሳሳተ መንገድ በመከተል ሕዝባችንን ለችግር ዳርገናል ፤ በዚህ በመፀፀት የበደልነውን ሕዝብ በልማት ለመካስ ተዘጋጅተናል ሲል ገልጿል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ እንደገለጹት፤ የዞኑን ብሎም የክልሉን ሰላም ለማፅናት በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው።
መንግስት የሰጣቸውን የሰላም እድል እንዲጠቀሙ በተደረገው ጥረት የሰላም አማራጭን በመቀበል ቀደም ሲል የተመለሱ የተሃድሶ ስልጠና ተሰጥቷቸው ህይወታቸውን እየለወጡ መሆኑን አስረድተዋል።
አሁንም የሰላም አምባሳደር ሆነው የመጡ የቀድሞ ታጣቂዎችን የዞኑ መስተዳድርና ሕዝብ አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት በፈለጉት የሙያ መስክ እንዲሰማሩ ይደረጋል ብለዋል።
በመከላከያ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የ504ኛ ኮር ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ቾቤ ወርቁ በበኩላቸው፤ መንግስት ለሰላም ሁሌም በሩ ክፍት ነው ብለዋል።
ሕብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት መረጃ በመስጠትና ችግር ወስጥ የገቡትን ወደ ሰላም እንዲመጡ በማድረግ እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበው ፤ በቀጣይም ይህ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።